ኢትዮጵያ ቡና ኒቦሳ ቩሲቪችን አሰልጣኝ አድርጎ ቀጥሯል

ኢትዮጵያ ቡና አዲስ አሰልጣኝ መቅጠሩን ዛሬ በይፋዊ የፌስቡክ ገፁ ገልጿል፡፡ ከሰርቢያዊው አሰልጣኝ ድራጋን ፖፓዲች ጋር በውድድር ዓመቱ የተለያየው ቡና ዳግም ፊቱን ወደ የውጪ ሃገር አሰልጣኝ አዙሯል፡፡

ክለቡን ለማሰልጠን ሰትዋርት ሃልን ጨምሮ የተለያዩ አሰልጣኞች የተወዳደሩ ቢሆንም የክለቡ ቦርድ የ54 ዓመቱን ሰርቢያዊ ኒቦሳ ቩሲቪችን ምርጫው አድርጓል፡፡ ቩሲቪች ወደ አዲስ አበባ ዛሬ ጠዋት መድረሳቸው እና የቅድመ ውድድር ዘመን ዝግጅትን ለመጀመር ወደ ሃዋሳ የተጓዘውን ክለቡን እንደሚቀላቀሉ ክለቡ ጨምሮ ገልጿል፡፡

ቩሲቪች ወደ አፍሪካ በአሰልጣኝነት ሲመጡ ይህ ለሁለተኛ ጊዜያቸው ሲሆን ከዚህ ቀደም የጋናውን ሃያል አክራ ሃርትስ ኦፍ ኦክን ማሰልጠን ችለዋል፡፡

በተጫዋችነት ዘመናቸው የአጥቂ አማካይ የነበሩት ቩሲቪች ከ1981-1998 ድረስ እግርኳስ ቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ፣ዩናይትድ ስቴትስ፣ ደቡብ ኮሪያ እና ስሎቬኒያ የተጫወቱ ሲሆን የአሰልጣኝነት ህይወታቸውን በ2002 ነበር የጀመሩት፡፡ ቩሲቪች ሃርትስ ኦፍ ኦክን ለአንድ የውድድር ዘመን ያሰለጠኑ ሲሆን የአክራው ክለብ ቀንደኛ ደጋፊዎች ክለቡ ካለበት መጥፎ የውጤት ቀውስ ማውጣት ባለመቻለቸው ከፍተኛ ተቋውሞ ደርሶባቸው ነበር፡፡ ይህ ተቋውሞ አሰልጣኙ ከክለቡ እንዲባረሩ ያስቻለ ሲሆን ወደ ሃገራቸው ሰርቢያ ተመልሰው በሶስተኛ ዲቪዝዮን የሚወዳደረውን ቲሞክን አሰልጥነዋል፡፡

ሃርትስ ኦፍ ኦክ ቩሲቪችን ከመቅጠሩ በፊት ከድራጋን ፖፓዲች ጋር ድርድር ላይ የነበረ ሲሆን አሰልጣኙ ወደ ቡና እንዲመጡ የፖፓዲች ሚና እንዳለበት ተነግሯል፡፡ ቡና የአሰልጣኙን የውል፣ ደሞዝ እና ጥቅማጥቅም ሁኔታዎች ከመግለፅ ተቆጥቧል፡፡

Leave a Reply