የኢትዮዽያ ከ17 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን በአፍሪካ ከ17 አመት ዋንጫ ማጣርያ ከግብጽ ጋር የመልስ ጨዋታውን ያደርጋል፡፡
በአሰልጣኝ አጥናፉ የሚመራው ታዳጊ ብሄራዊ ቡድን ከካይሮ በ3-1 ድል ከተመለሰ በኋላ ወደ ድሬደዋ በማቅናት ለመልሱ ጨዋታ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል፡፡
በራስ ሆቴል በመክተም ልምምዱን ከጀመረ 8ኛ ቀኑን የያዘው ታዳጊ ቡድኑ በጥሩ ፍላጎት እና መነሳሳት ልምምዳቸውን ሲሰሩ ለማየት ችለናል፡፡ ማጥቃትን መሰረት ያደረገ አጨዋወት ፣ ለሁለት ተከፍሎ በግማሽ ሜዳ መጫወት እና የቆሙ ኳሶችን አክርሮ የመምታት ልምምዶች የዛሬው መርሃ ግብራቸው አካል ነበር፡፡
በድሬዳዋ ያለውን ከፍተኛ ሙቀት መላመድ ተስኗቸው የተወሰኑ ተጨዋቾች የመንሰር ችግር አጋጥሟቸው በህክምና ባለሙያ ድጋፍ ሲደረግላቸውም አይተናል፡፡
ተጋጣሚው የግብፅ ብሔራዊ ቡድን 35 የልኡካን ቡድን በመያዝ ነገ ጠዋት አአ በመግባት ወድያው ወደ ድሬዳዋ እንደሚያቀና የሚጠበቅ ሲሆን ሳምራን ሆቴል ማረፊያው እንደሚሆን ለማወቅ ችለናል፡፡ ጨዋታውን የሚመሩት አራቱም ዳኞቹ ሱዳናውያን ሲሆኑ ኮሚሽነሩ ደግሞ ከኬንያ ነው፡፡
የኢትዮጵያ እና የግብጽ ከ17 አመት በታች ብሄራዊ ቡድኖች የመልስ ጨዋታ በመጪው እሁድ ድሬዳዋ ስታድየም ላይ ይደረጋል፡፡ የድሬደዋ ስታድየም የተመልካች ቁጥር አቅሙን ለማሳደግና በተለምዶ በካታንጋ እና ጥላ ፎቁ ግራና ቀኝ የስታድየሙ ክፍል ተጨማሪ መቀመጫዎችን ለመስራት ግንባታው እየተፋጠነ መሆኑን ለማየት ችለናል፡፡