የአአ ከተማ ተጫዋቾች ስለ ውድድር ዘመኑ ስኬታቸው እና የቀጣይ አመት እቅዳቸው. . .

የ2008 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ሊጠናቀቅ ተቃርቧል፡፡ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ የተላቀሉት አራት ክለቦች ከወዲሁ የተለዩ ሲሆን ከነዚህም መካከል በምድብ ለ የሚገኘው አዲስ አበባ ከተማ ከ2 ሳምንት በፊት ወደ ሊጉ ማደጉን አረጋግጧል፡፡

ክለቡ በሚከተለው በኳስ ቁጥጥር ላይ ያመዘነ እንቅስቃሴ ላይ ውበት እንዲላበስ ቁልፍ ሚና እየተወጣ የሚገኘው ባለ ክህሎቱ አማካይ ሙሃጅር መኪ ስለ ውድድር ዘመኑ ጉዟቸው ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠው አስተያየት የስብስባቸው ጥንካሬ ለስኬት እንዳበቃቸው ገልጿል፡፡

“ውድድሩ ብዙ ልፋት የሚጠይቅ ነበር፡፡ ብዙ ችግሮች ነበሩብን ፤ ነገር ግን ክለቤ ጠንካራ ስብስብ ስለያዘ የውድድሩን ፈተናዎች በህብረት ማለፍ ችለናል፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ የአሰልጣኞቹ ስታፍ ጠንካራ ነበር ፤ እነሱ ጋር ያለው ጥንካሬ እኛን በበለጠ አጠናክሮናል፡፡

” በቀጣይ አመት እንደ ሌሎቹ የፕሪምየር ሊግ ክለቦች በቂ እረፍት ሳናደርግ ሊጉን መጀመራችን ሊከብደን ይችላል፡፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ ያደረገው የከፍተኛ ሊግ ውድድሩ ዘግይቶ መጀመሩ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ተጠያቂው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ነው፡፡ የመርሃ ግብር አወጣጡ በጣም የሚያስቸግር ነው ይህንን ችግር ባለን ብርታት እኛ ተቋቁመነዋል፡፡ ነገር ግን በቀጣይ አመት ለሚሳተፉት ክለቦች ይህ የማይሻሻል ከሆነ ክለቦችን የሚጎዳ ነገር ነው’’፡፡ ይላል፡፡

PicsArt_1471606471671

የቡድኑ ሌላኛው ኮከብ ዘሪሁን ብርሃኑም የአምበሉን አስተያየት በማጠናከር የከፍተኛ ሊግን ፈተና ያብራራል፡፡

” ሁሉም እንደሚያውቀው ውድድሩ ዘግይቶ ነው የጀመረው፡፡ ይህ ደግሞ የጨዋታ መደራረብ እንዲያጋጥመን አድርጎታል፡፡ የውድድሩ ፎርማት አንድ ቡድን በአመቱ ውስጥ ቢያንስ 30 ያክል ጨዋታዎችን እንዲያደርግ ያስገድዳል፡፡ በዛ ላይ ደግሞ ለወጣት ብሄራዊ ቡድን ከክለቡ የተመረጥን ተጨዋቾች ስለነበርን ጨዋታዎች በተያዘላቸው መርሃ ግብር እንዳይከናወኑ እና ተስተካካይ ጨዋታዎች ወደ ክረምት ጊዜው ተገፍቶ እንድናከናወን ተገደናል፡፡ ይህ ደግሞ በአመቱ የተፈተንበት ክስተት ሆኗል’’

የከፍተኛ ሊጉ ክለቦች ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ለማደግ ይረዳናል የሚሉትን ስትራቴጂ ተግብረዋል፡፡ ወልድያ እና ፋሲል ከተማ የፕሪሚየር ሊግ ልምድ ያላቸው በርካታ ተጫዋቾችን በቡድናቸው በማካተት ስኬት ሲያስመዘግቡ ጅማ አባ ቡና እና አአ ከተማ ደግሞ አመዛኙ ስብስባቸውን በወጣት ተጫዋቾች በማዋቀር ወደ ሃገሪቱ ትልቅ ሊግ ማደግ ችለዋል፡፡

ሁለቱ የአአ ከተማ ተጨዋቾችም በዚህ ይስማማሉ፡፡ በቡድኑ ውስጥ አብዛኞቹ ተጨዋቾች በተመሳሳይ እድሜ ላይ ስለሚገኙ ለመቀራረብ እንደረዳቸው እና ለቡድን ህብረትም እንደጠቀማቸው ያምናሉ፡፡ ይህ ደግሞ ለስኬታቸው ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በውድድር ዘመኑ የተመልካችን ቀልብ የሚስብ እንቅስቃሴ በማሳየት አአ ከተማ ተጠቃሽ ክለብ ነበር፡፡ ይህንን በቀጣዩ አመት ይዘው እንደሚቀጥሉም ዘሪሁን ያምናል

” ቡድናችን ጠንካራ ነው፡፡ በቀጣይ አመት ደግሞ የማናቀው ሊግ ውስጥ ስለሆነ የምንገባው በሊጉ ላይ ልምድ ያላቸውን ተጨዋቾች ከክለብ አሰልጣኞቻችን ጋር በመነጋገር ጨምረን ሰዎችን በውብ እግር ኳስ የሚያዝናና ፣ እንደስሙ አዲስ የሆነ ቡድን ይዘን ለመምጣት እንደ ቡድንም እኔም በግሌ ጥረት እናደርጋለን”፡፡

PicsArt_1471606409077

ሙሃጅር መኪ በበኩሉ በቀጣዩ አመት ተሻሽለው ለመቅረብ እንደሚጥሩ ገልጿል፡፡

” በዚህኛው አመት እቅዳችንን አሳክተናል፡፡ በሚቀጥለው አመትም በሊጉ ላይ ተፎካካሪ ቡድን ለማቅረብ እንጥራለን፡፡ ሁሉም ቡድን ከአመት አመት ይታደሳል ፤ ማሻሻያ ይደረግለታል፡፡ እኛም ያሉብንን ክፍተቶች ከአሰልጣኞቻችን ጋር እየተመካከርን ስህተቶቻችንን አሻሽለን ሊጉ ላይ እድሜያችንን ለማራዘም እንሞክራለን’’፡፡

Leave a Reply