” የስኬታችን ዋና ምስጢር ጠንክረን መስራታችን ነው” የወልድያ አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ

በ2007 ከፕሪሚየር ሊጉ የወረደው ወልድያ በአዲስ መልክ በተዋቀረው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የዘንድሮ የውድድር ዘመን 3 ጨዋታ እየቀረው በአመቱ ወደ ፕሪሚየር ሊግ መመለሱን አረጋግጧል፡፡

ወልድያ ወደ ሊጉ ለመመለስ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾችን ከማሰባሰቡ በተጨማሪ የቀድሞው የመከላከያ እና ደደቢት አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ትልቁን ሚና ተጫውተዋል፡፡

በመጀመርያ የወልድያ የውድድር ዘመናቸው ክለቡን ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ያሳደጉት አሰልጣኝ ንጉሴ የከፍተኛ ሊጉን ፈታኝነት ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል፡፡

“በአዲስ መልክ የተጀመረው የከፍተኛ ሊግ ውድድር ከብዙ አቅጣጫዎች ስናየው አስቸጋሪ እና ከባድ ነው፡፡ ከጨዋታዎች መደራረብ ፣ ከሜዳዎች አለመመቸት እና ከመሳሰሉት አንፃር በጣም ከባድ ውድድር ነው፡፡ ነገር ግን የያዝነው ቡድን ጠንካራ ስለነበር ፈተናዎቹን በአግባቡ መወጣት ችለናል፡፡

“ከምንም በላይ ችግር የሆነብን የሜዳዎች አለመመቸት ነው፡፡ ብዙ የክልል ሜዳዎች ለመጫዎት አይመቹም፡፡ ይህ ችግር በሜዳችን እንደተጫወትነው የጨዋታ እንቅስቃሴ ከሜዳችን ውጪም እንዳንጫወት አድርጎናል፡፡ ነገር ግን በሊጉ ላይ ያሉ ክለቦች ያሳዮት የነበረው እንቅስቃሴ በጣም በጣም ጥሩ ነበር፡፡ በተለይ በአማራ ክልል ክለቦች መካከል የነበረው የተፎካካሪነት መንፈስ እኛን አጠንክሮናል፡፡” ይላሉ፡፡

አሰልጣኝ ንጉሴ የቡድኑ ስኬት ምስጢር የሚሉትንም ያብራራሉ፡፡

” ዋነኛ የስኬታችን ሚስጥር ጠንክረን መስራታችን ነው፡፡ ተጨዋቾቼ በአግባቡ የሚሰጣቸውን ስልጠና ይወስዳሉ ፤ ሜዳ ላይም በደንብ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ ቡድኑ የአሸናፊነት መንፈስ እንዲኖረው ሙሉ ቡድኑን በህብረት ለማቀናጀት እንሞክራለን፡፡ ይሄ ነው እንግዲ ወነኛ የስኬታችን ቁልፉ ሚስጥር” የሚሉት አሰልጣኝ ንጉሴ ደጋፊዎቻቸው እና የሜዳ አድቫንቴጅ መጠቀማቸውም ለስኬታማነታቸው ቁልፍ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

“እንደሚታወቀው በመጀመርያው ዙር በሜዳችን ምንም ጨዋታ አልተሸነፍንም ፤ ጎልም አልተቆጠረብንም ፤ በዲሲፕሊንም ረገድ ምንም አይነት የማስጠንቀቂያ ካርድ ሳናይ ነበር የጨረስነው፡፡ ይህ ደግሞ  ምን ያክል ቡድናችን ጠንካራ እንደነበር ያስረዳል፡፡

“ደጋፊዎቻችን እጅግ ሊመሰገኑ ይገገባል፡፡ ከልምምድ ጀምሮ እስከ ክልል ጨዋታዎች ድረስ ከጎናችን ሆነው እንደ 12ኛ ተጫዋች ቡድኑን ሲያበረታቱት ነበር እና ደጋፊዎቻችን ለኛ ስኬት ሌላኛው ምክንያት ናቸው፡፡”

ወልድያ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ባደገ በአመቱ ወየ ከፍተኛ ሊግ ወርዷል፡፡ አሁን ደግሞ ያለፈ በድጋሚ ላለመውረድ ሁለተኛ እድል አግኝቷል፡፡ አሰልጣኝ ንጉሴም ከፈተናዎች ጋር በመጋፈጥ ለቀጣዩ አመት ቡድናቸውን እንደሚያዘጋጁ ተስፋ አድርገዋል፡፡

“በቀጣይ አመት ቡድኑን ለማጠናከር የተቻለንን እናደርጋለን፡፡ ነገር ግን ሌሎች የፕሪምየር ሊጉ ክለቦች የቅድመ ውድድር መርሃ ግብራቸውን ጀምረዋል፡፡ ነገር ግን እኛ ገና ያሉብንን ጨዋታዎች አልጨረስንም፡፡ ሌሎቹ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ደግሞ በቂ እረፍት አግኝተው የቀጣይ አመት እቅዳቸውን ከወዲሁ ያመቻቻሉ፡፡ እኛ ግን ለእንደዚህ አይነቱ ጉዳይ አልታደልንም፡፡

“ክለቤ ላይ ያለውን ክፍተት እንኳን ለማስተካከል አዳዲስ ተጨዋቾች ማስፈረም ይገባን ነበር፡፡ ነገር ግን የተጨዋቾች የዝውውር መስኮት እንኳን ከተከፈተ ጀምሮ ባለው ረጅም ጊዜ ብዙ ተጨዋቾች በሌሎች ክለቦች ተመርጠው አልቀውብናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ተጠያቂው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ነው፡፡ ፌደሬሽኑ እንደዚህ አይነት አሰራሮችን ካላስተካከለ ከታች የሚያድጉ ክለቦችን በጣም ነው የሚጎዳን፡፡ ነገር ግን የተቻለንን አድርገን ቡድናችንን ለማሻሻል ጥረት እናደርጋለን፡፡”

አሰልጣኝ ንጉሴ በመጨረሻም የወልድያን የ2009 የውድድር ዘመን እቅድ ያብራራሉ፡፡

” ዋነኛ የቀጣይ አመት እቅዳችን በፕሪምየር ሊጉ ላይ ለመቆየት ነው፡፡ እንደ 2007ቱ ሊጉን ተቀላቅለን ወዲያው ላለመውረድ ከፍተኛ ስራዎችን ከክለቡ አመራሮች ጋር እየተነጋገገርን ለመስራት  እንሞክራለን፡፡”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *