ስለ ወልድያ የውድድር ዘመን ስኬት ተጫዋቾቹ ምን ይላሉ?

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የ2008 የውድድር ዘመን ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ያለፉትን ክለቦች ለይቷል፡፡ ወልድያም ከ2 ሳምንት በፊት ወደ ሊጉ ማደጉን አረጋግጧል፡፡

ለቡድኑ ስኬታማነት ቁልፍ ሚና ከተወጡት መካከል አንጋፋው የቡድኑ አምበል ዮሃንስ ኃይሉ እና ግብ አዳኙ እዮብ ወልደማርያም ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያደረጉትን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

“የስኬታችን ምስጢር አንድነታችን ነው” ዮሃንስ ኃይሉ

ስለ ውድድር ዘመኑ

“አመቱን ያሳለፍኩት እጅግ ደስተኛ ሆኜ ነው፡፡ እኔ ብቻ ሳልሆን ሁሉም የቡድኑ ስብስብ በጣም ደስተኛ ሆኖ ነበር አመቱን ያሳለፈው፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋና ምክንያታችን እርስ በእረስ ያለን መቀራረብ እና መከባበራችን ነው፡፡ በዛ ላይ ደግሞ ውጤታችንም ጥሩ ስለነበር አመቱን ደስተኛ ሆነን ነው ያሳለፍነው፡፡”

ስለ ምድብ ሀ

“ምድባችን በጣም ከባድ ነበር ፤ ሁሉም እኛ ምድብ ያሉ ቡድኖች ፈታኝ ነበሩ፡፡ ጥሩ ጥሩ ተጨዋቾች አሉዋቸው፡፡ ነገር ግን እኛ ቡድን ውስጥ ያሉት ተጨዋቾች እኔን ጨምሮ አብዛኞቹ ተጨዋቾች ልምድ አለን፡፡ እንዴት ጨዋታዎችን ማሸነፍ እንደምንችል በአግባቡ እናውቃለን ለዛም ነው ብዙ ጨዋታዎችን ያሸነፍነው”

የስኬት ምስጢር

“ዋነኛ የስኬታችን ሚስጥር አንድነታችን ነው፡፡ ሁላችንም ለአንድ አላማ ስለቆምን በህብረት አላማችንን ለማሳካት ስለምንጥር ነው ለዚህ ስኬት የበቃነው”

የቀጣይ አመት እቅድ

” የቀጣዩ አመት የግል እቅዴ እዚሁ ቡድን ውስጥ መቆየት እና የተቻለኝን ሁሉ ለክለቤ ማድረግ ነው፡፡ እንደ ቡድን ደግሞ በቀጣይ አመት ክለቤ በሊጉ ላይ ተፎካካሪ እንዲሆን እና በሊጉ ላይ ለመቆየት እንሞክራለን”

PicsArt_1471684443718

“በሊጉ ከባድ ፈተና ሊያጋጥመን እንደሚችል እገምታለው” እዮብ ወልደማርያም

ስለ ውድድር ዘመኑ

” ያሳለፍነው ውድድር በጣም ከባድ ነበር፡፡ ሁሉም ክለብ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለማለፍ ጠንክሮ ነው የሚሰራው ፤ በተለይ ደግሞ እኛ ምድብ ያሉ ቡድኖች እጅግ ጠንካራ ነበሩ፡፡ ትልልቆቹ ክለቦች ብቻ ሳይሆን ላለመውረድ የሚጫወቱት ክለቦች በራሱ የዋዛ አደሉም፡፡ ነገር ግን እኛ በአግባቡ ጨዋታዎችን እያሸነፍን እቅዳችንን አሳክተናል”

ፈተናዎች

“ለኛ ለተጨዋቾች ችግር የነበረብን ርቀት ያላቸው የክልል ሜዳዎች ሄደን ጨዋታዎችን ማድረግ ነበር፡፡ በዛ ላይ በቂ እረፍት ሳናደርግ እረፍታችንን በጉዞ እየጨረስን በጣም ተዳክመን ነው አንዳንድ ጨዋታዎችን ያደረግነው፡፡ ይህ እኛን አዳክሞን እደፈለግነው አቅማችንን አውጥተን እንዳንጫወት አድርጎናል፡፡ በዛ ላይ የሜዳዎችም ችግር አለ፡፡ እንዚህ  እነዚህ ምክንያቶች በአመቱ ችግር ሆውብን ነበር”

ደጋፊዎች

” ደጋፊዎቻችን ሁሌም ከኛ ጋር ነበሩ፡፡  ስናሸንፍም ስንሸነፍም ሁሌ ያበረታቱን ነበር፡፡ ለነዚህ ደጋፊዎቻችን ክብር ይገባቸዋል፡፡ አሰልጣኞቻችንም በጣም ጥሩዎች ነበሩ ፤ እኛ ያለንን ብቃት ለማውጣት የተመቸ አጨዋወት ያዘጋጁልን ነበር”

ቀጣይ አመት

” በግሌ በቀጣይ አመት ኮንትራት አለኝ ፤ እዚሁ የምቆይ ይመስለኛል፡፡ በሊጉ ከባድ ፈተና ሊያጋጥመን እንደሚችል እገምታለው እና በዚኛው አመት ካሳለፍኩት አመት የተሻለ ለመሆን ጠንክሬ እሰራለው፡፡ እንደቡድንም አዳዲስ ተጨዋቾችን ጨምረን በሊጉ ላይ ጥሩ ነገር ለማሳየት እንሞክራለን”

ያጋሩ

Leave a Reply