የኢትዮጵያ U17 ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ አጥናፉ ስለ መልስ ጨዋታው ይናገራሉ

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን ከሜዳው ውጪ ካይሮ ላይ የግብፅ አቻውን ከሁለት ሳምንት በፊት 3-1 በማሸነፍ ማዳጋስካር ለምታሰናዳው የቶታል የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ ሁለተኛ የማጣሪያ ዙር ለማለፍ የተሻለ ዕድል ይዘዋል፡፡

የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ አጥናፉ አለሙ የግብፁ ጨዋታ ደካማ እና ጠንካራ ጎናቸውን ለማየት እንዳገዛቸው ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል፡፡

“ከመጀመሪያው ሃዋሳ ላይ ጥሩ ዝግጅት አድርገናል፡፡ በመሆኑም ከግብፅ ጋር ለነበረን ጨዋታ ጥሩ እገዛን አድርጎልናል፡፡ የግብፁ ጨዋታ ለኛ ጥሩ ነበር ፤ የቡድናችን ጠንካራ እና ደካማ ጎን እንድናይ እና ደካማ ጎናችንን እንድናርም ጥሩ አጋጣሚን ፈጥሮልናል፡፡ በመሆኑም እንግዲህ ይህንን ውጤት ለማስጠበቅ ጥሩ ዝግጅት አድርገናል፡፡”

አሰልጣኝ አጥናፉ ቡድናቸው በካይሮው ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ አፈግፍጎ መከላከልን የመረጠው የጨዋታውን ውጤት ለማስጠበቅ ነበር ብለዋል፡፡ “ይህ እንግዲህ ከጉጉት ነው፡፡ ሁለተኛው ያለውን ውጤት ለማስጠበቅ ነው፡፡ ለምን ቢባል ከሜዳ ውጪ ጨዋታ ስለነበር አቻ ወይም ማሸነፍ ሁሌም በሜዳ ለምታደርገው ጨዋታ የበላይነት ይሰጥሃል፡፡ ያንን ማድረጋችን በተወሰነ ደረጃ ትክክል ነበርን፡፡” ያሉት አሰልጣኝ አጥናፉ በኢትዮጵያ ያልታሰበ ሽንፈት የደረሰባት ግብፅ ድሬዳዋ ላይ አጥቅተው ለማሸነፍ ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ገምተዋል፡፡

“በዕርግጠኝነት የማጥቃት ጨዋታ ተጫውተው ውጤቱን ለመቀየር እንደሚመጡ እናውቃለን፡፡ ለዚህ ደግሞ እኛ መከላከል አይጠበቅብንም፡፡ እኛም አጥቅተን መጫወት እንፈልጋለን ምክንያቱም 90 ደቂቃ መከላከል አስቸጋሪም ነው አስፈላጊም አይደለም፡፡ ይሁንና በፊት የሰጡን ግምት ዝቅተኛ መሆኑ ጠቅሞናል፡፡ ምክንያቱም ውጤቱን አልጠበቁትም፡፡ አይተህ ከሆነ ሁለቱ ግቦች በመልሶ ማጥቃት ነው ያስቆጥርነው፡፡ ሁለት ያለቀላቸውን ኳሶች አምክነናል፡፡ እነሱም በጣም አጥቅተውናል፡፡ ይህ ቀላል ፈተና አይሆንም ምክንያቱም እነሱ አንድ እድል ነው ያላቸው፡፡ ዕድላቸውን እንዳይጠቀሙ ዘግተን መጫወት ነው ያለብን በተለይ በኛ ሜዳ ላይ ኳስን እንዳይጫወቱ ጥሩ ዝግጅት አድርገናል፡፡”

አሰልጣኙ በዕሁዱ ጨዋታ እንደሚያሸንፉና የቡድኑ የመንፈስ በጥሩ ሆኔታ ላይ እንዳለ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *