” በመልሱ ጨዋታ ጥሩ ውጤት እንጠብቃለን” የግብፅ U-17 አሰልጣኝ ያስር መህመዲን

የግብፅ ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን ከኢትዮጵያ ጋር ላለበት የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታ አርብ ወደ ድሬዳዋ ተጉዟል፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት ካይሮ ላይ ያልተጠበቀ ሽንፈትን የቀመሰው ብሄራዊ ቡድኑ የአንድ ተጫዋችን ብቻ ለውጥ አድርጎ ነው ለመልሱ ፍልሚያ የተዘጋጀው፡፡

የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ያስር መሃመዲን ለመሎሱ ጨዋታ በጠንካራ ሁኔታ እንደተዘጋጁ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ “ከመጀመሪያው ዙር ጨዋታ በኃላ በጠንካራ ሁኔታ ስንዘጋጅ ነበር፡፡ ካይሮ ላይ ባለ ካምፕ ለአንድ ሳምንት ስንዘጋጅ ነበር፡፡ ጠንካራ ልምምዶችም የዝግጅቱ አካል ነበሩ፡፡ ጥሩ ውጤት ከፈጣሪ ጋር እንጠብቃለን፡፡” ብለዋል፡፡

አሰልጣኝ መሃመዲን አክለውም ብሄራዊ ቡድናቸው ለመልሱ ጨዋታ የወዳጅነት ጨዋታ አለማድረጉ እንደክፍተት ተመልክተውታል፡፡ “ከኢትዮጵያው ጨዋታ በፊት 11 የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን መጫወት ችለናል፡፡ ይህም በቂ አልነበረም ምክንያቱም ይህ ቡድን በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ የተሰራ ነው፡፡ ለመልሱም ጨዋታ የአቋም መለኪያ ጨዋታ ማድረግ አልቻልንም፡፡”

ያም ሆኖ አሰልጣኙ በመልሱ ጨዋታ ቡድናቸው ጥሩ ውጤት እንደሚያመጣ ተስፋ አድርገዋል፡፡ “ጥሩ ውጤት እንደሚመጣ ተስፋ አለኝ፡፡ የመጀመሪያውን ጨዋታ ተመልክተህ ከሆነ ስድስት ወይም ሰባት የሚሆኑ የግብ ዕድሎችን አምክነናል፡፡ በተለይ በጨዋታው የመጀመሪያ አምስት ደቂቃዎች፡፡ በነዚህ ደቂቃዎች ሶስት ወይም አራት ግቦች ማስቆጠር እንችል ነበር፡፡” ሲሉ አስተያየታቸውን አጠቃለዋል፡፡

PicsArt_1471698152822

የቡድን መሪው ታሃ ሰዒድ በበኩላቸው በጥሩ ሁኔታ እንደተዘጋጁ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ “ካምፕ ውስጥ ሆነን ነው ዝግጅት ያደረግነው፡፡ ለተጫዋቾቻችን ከኢትዮጵያው ግጥሚያ በኃላ የሶስት ቀን እረፍት ሰጥተን ነበር ዳግም ወደ ዝግጅት የገባነው፡፡”

ሰዒድ የድሬዳዋ ስታዲየም የመጫወቻ ሜዳን ምቹ አለመሆኑንም ተናግረዋል፡፡ “ሜዳው በጣም መጥፎ ነው፡፡ ይቅርታ አድርግልኝ፡፡ ግብፅ ላይ ፔትሮስፖርት ስታዲየም ነበር የተጫወትነው፡፡ ፔትሮስፖርት ጥራት ያለው ኢንተርናሽናል ስታዲየም ነው፡፡ እዚህ ሜዳው በአጠቃላይ ጥሩ አይደለም፡፡” የሚሉት ሰዒድ ጨምረውም በመልሱ ጨዋታ የተሻለ ውጤት ይዘው እንደሚመለሱ ገልጸዋል፡፡ “ደጋፊዎች በመጀመሪያው ዙር ግጥሚያ ውጤት እንደተበሳጩ እናውቃለን፡፡ ጥሩ እንሰራለን ብለን እናስባለን፡፡ ፌድሬሽናችን የነገው ጨዋታ ውጤት አይደለም ማየት የሚፈልገው ምክንያቱም ይህ ቡድን በሚቀጥሉት ጥቂት አመታት ወደ ዋናው ብሄራዊ ቡድን የሚያድጉ ተጫዋቾችን የያዘ ስብስብ ነው፡፡”

አል አሃሊ ሰባት፣ ኢኤንፒፒአይ አምስት እና ዛማሌክ አንድ ተጫዋቾችን ለግብፅ ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን ማስመረጥ ችለዋል፡፡

Leave a Reply