ሽመልስ በቀለ ሐሙስ ወይም አርብ ብሄራዊ ቡድኑን ይቀላቀላል

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በ2017 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ የመጨረሻ የምድብ ጨዋታ ከሲሸልስ ጋር ለሚያደርገው ጨዋታ በሀዋሳ የሚያደርገውን ዝግጆት ቀጥሏል፡፡ እስካሁን ቡድኑን ያልተቀላቀሉት ሸመልስ በቀለ እና ዋሊድ አታም በቀጣዮቹ ቀናት ቡድኑን ይቀላቀላሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ ያደረገው ሽመልስ የብሄራዊ ቡድኑን ዝግጅት ለመቀላቀል የሚጠብቀው የክለቡን ፍቃድ እንደሆነ ተናግሯል፡፡

” በአሁኑ ሰአት የክለብ ውድድር የለም ፤ ዝግጅት ብቻ ነው፡፡ ቶሎ መጥቼ ብቀላቀል ደስ ይለኛል፡፡ ሆኖም ክለቡ በፊፋ ካሌንደር ስለሚመራ ጨዋታው አንድ ሳምንት ሲቀረው ነው የሚለቀኝ፡፡ ዛሬ ለክለቡ ጥያቄ አቀርብና በእርግጠኝነት ሀሙስ ወይም አርብ ብሄራዊ ቡድኑን እቀላቀላለሁ” ብሏል፡፡

በግብፅ እየያሳለፈ ባለው የእግርኳስ ህይወቱ ደስተኛ እንደሆነ የሚገልፀው ሽመልስ መልካም የቅድመ ውድድር ዝግጅት እያሳለፈ እንደሆነ ገልጿል፡፡

” ጳጉሜ 5 ለሚጀምረው አዲሱ የግብፅ ፕሪሚየር ሊግ ዝግጅት ከጀመርን 1 ወር ሆኖናል፡፡ ለ15 ቀን አሌሳንድሪያ በቀን ሁለቴ እና ሶስት ጊዜ የልምምድ ጊዜ የነበረን ሲሆን አሁን ወደ ካይሮ በመመለስ ዝግጅታችንን ጠንክረን እየሰራን እንገኛለን፡፡

” ክለቡ የተሻለ ውጤት ለማምጣት አዳዲስ ተጨዋቾችን በየአመቱ ያስመጣል፡፡ ያው በአዲሱ የውድድር ዘመን የሚከሰተውን ሊጉ ሲጀመር የምናየው ይሆናል፡፡ “ ሲል ሃሳቡን አጠቃሏል፡፡

በተያያዘ ዜና እስካሁን ብሄራዊ ቡድኁን ያልተቀላቀለው የኦስትራንድስ ተከላካይ ዋሊድ አታ በዚህ ሳምንት መጨረሻ ይቀላቀላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከቡድኑ ዝግጅት ጋር በተያያዘ በልምምድ ላይ ጉዳት ያጋጠመው አብዱልከሪም መሃመድ ከጉዳቱ አገግሞ ትላንት ልምምድ የጀመረ ሲሆን ከአቤል ማሞ በስተቀር ሁሉም በተሟላ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡

ሀዋሳ ኢንተርናሽናል ስታድየም ላይ የሚደረገው የኢትዮጵያ እና ሲሸልስ ጨዋታ ለመጪው ነሀሴ 27 ፕሮግራም ተይዞለት የነበረ ቢሆንም የአንድ ቀን ሽግሽግ ተደርጎበት ለቅዳሜ ነሀሴ 28 ቀን 2008 ቀጠሮ ተይዞለታል፡፡

Leave a Reply