የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የሴቶች ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ አድርጎ መሰረት ማኔን የቀጠረው ከሳምንታት በፊት ነበር፡፡ አሰልጣኝ መሰረት ከድሬዳዋ ከተማ በዓመቱ መጨረሻ የተለያየች ሲሆን በመጪው መስከረም በዩጋንዳ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ ተሳታፊ የሚሆኑትን ሉሲዎቹን የምትመራ ይሆናል፡፡ አሰልጣኝ መሰረት ስለብሄራዊ ቡድኑ ዝግጅት፣ ሊመዘገብ ስለታሰበው ውጤት እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ድሬዳዋ ላይ አጠር ያለ ቆይታ አድርጋለች፡፡
ለሴቶች ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት መመረጥን ጠብቀሽው ነበር?
አዎ ጠብቄው ነበር፡፡ ገና ድሬዳዋ ከተማን በያዝኩበት ጊዜ ነበር ስለብሄራዊ ቡድን የማስብ የነበረው፡፡ የጠበቅኩት ነገር ነበር፡፡
ዝግጅት ዕሁድ ዕለት ነበር የጀመራችሁት፡፡ የዝግጅት ዕቅድሽ ምን ይመስላል?
ለአንድ ሳምንት በቀን ሁለቴ ጠንከር ያለ ልምምድ እንሰራለን፡፡ ተጫዋቾቹ ከዕረፍት ስለተመለሱ ፊትነሳቸውን ዳግም ማግኘት አለባቸው፡፡ ከአንድ ሳምንት በኃላ ወደ መደበኛ ልምምድ የምንገባ ይሆናል፡፡ ያለው ግዜ አጭር ስለሆነ የአቋም መለኪያ ጨዋታ ከሌላ ሃገር ጋር ማድረግ አስቸጋሪ ነው፡፡ ቢሆንም ወደ መደበኛ ልምምድ ከገባን በኃላ ሁለት የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች ድሬዳዋ ከሚገኙ የወንድ ቡድኖች ጋር የምናደርግ ነው የሚሆነው፡፡ ለ31 ተጫዋቾች ነበር ጥሪ ያደረግነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ቅድስት ቦጋለ እና ሃብታም እሸቱ በግል ጉዳይ ከብሄራዊ ቡድኑ ውጪ ናቸው፡፡ ከልምምድ ባሻገር እንደዕቅድ የያዝኩት ባለሙያዎችን እየጋበዝኩ በስነ-ልቦናም እንዲጠነክሩ አስበናል፡፡ በተረፈ የልጆቹ የመስራት ፍላጎት እና መነሳሳት ጥሩ ነው፡፡
ከቡድኑ በተለዩት ሁለቱ ተጫዋቾች ምትክ ሌሎች ተጫዋቾች ይጠራሉ?
የልጆቹ ከቡድኑ መለየት ሌሎች ተጫዋቾችን እንዲጠሩ በር አይከፍትም፡፡ ልምምድ ላይ አይተን ክፍተት ካለ በተጠባባቂነት የያዝናቸው ተጫዋቾች ስላሉ እነሱን የምንጠራ ይሆናል፡፡ 23 ልጆችን ብቻ ይዘን ወደ ውድድር መሄድ ስላለበን በሂደት ተጫዋቾች የሚቀነሱ ይሆናል፡፡
የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ውጤት ከዓመት ዓመት እያሽቆለቀለ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን አስተያየት አለሽ?
ውጤቶቹ እንደሚባሉት አስከፊ አይደሉም፡፡ ደክመን ሳይሆን በጥቃቅን ስህተት ነው ወደ አፍሪካ ዋንጫ ማለፍ የተሳነን፡፡ የፌድሬሽኑ ፕሬዝደንት (አቶ ጁነዲ ባሻ) ዛሬ ጠዋት ቁርስ ላይ ተገኝተው ለተጫዋቾቹ የተናገሩት ይህንን ነው፡፡ ውጤት የጠፋው በአንዳንድ ጥቃቅን ችግሮች ምክንያት እንጂ ስለማንችል አይደለም፡፡
የብሄራዊ ቡደን ተጫዋቾች ምርጫ ጥያቄን አስነስቷል፡፡ ‘መሰረት የወንዶች እግርኳስ ላይ ስትሰራ ስለነበር በየትኛው መስፈርት ለሴት ብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾችን መረጠች’ የሚሉ ሃሳቦችም ይንሸራሸራሉ፡፡ ስለዚህ ሃሳብ ምን ትያለሽ?
ማንም ሰው የመሰለውን ነገር መናገር ይችላል፡፡ እሱ ባየበት መንገድ ነው ነገሮችን መረዳት የሚችለው፡፡ እኔ የልጆቹን ብቃት በደንብ አይቻለው፡፡ የደቡብ ምስራቅ ፕሪምየር ሊጉን ድሬዳዋ ስለነበርኩ የድሬዳዋ ከተማን ጨዋታዎች ተመልክቻለው፡፡ የወንዶች ፕሪምየር ሊግም ከሴቶች አስቀድሞ ስለተጠናቀቀ አዲስ አበባ ለስልጠና ስለተገኘው የሰሜን ማዕከላዊ ዞኑንም በቀን ሁለት እና ሶስት ጨዋታ ስለነበር ተመልክቻለው፡፡
በእግርኳስ ፌድሬሽኑ በኩል በሴካፋ ዋንጫው ላይ ቡድኑ ማስመዝገብ ስላለበት ውጤት ያስቀመጠው ግብ አለ?
በመጀመሪያ ደረጃ ፌድሬሽኑን ማመስገን እፈልጋለው፡፡ ፌድሬሽኑ እንደነዚህ ዓይነት ውድድሮች ላይ እንድንሳተፍ ስላደረገ ሊመሰገን ይገባል፡፡ ከ20 እና ከ17 ዓመት በታች ቡድኖች በውድድሮች እንዲገቡ ማድረጉ በጣም ጥሩ ነገር ነው፡፡ ሁልጊዜ ትችት አያስፈልግም፡፡ ሁልግዜ ትችት ለእግርኳሳችን የሚጠቅመው ምንድነው? መመስገን ያለበት መመስገን አለበት፡፡ በዚህ ስራ ላይ ሌላ ሰው ቢመረጥ አጋርነቴን ማሳየት አለብኝ፡፡ ፌድሬሽኑ ያስቀመጠልኝ ግብ አለ፡፡ ባያስቀምጥልኝም እንደባለሙያ ግብ ሊኖረኝ ይገባል፡፡ እኔ ብቻ ሳልሆን ተጫዋቾቼም ጨምሮ ግብ እንዲኖራቸው ተግሪያቸዋለው፡፡ ያው ግባችን ጥሩ ተፎካካሪ ሆነን ውጤት ለማምጣት ነው፡፡