ቻምፒየንስ ሊግ፡ ዋይዳድ ካዛብላንካ ምድብ አንድን በመሪነት ጨርሷል

የኦሬንጅ ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የምድብ የመጨረሻ ጨዋታዎች ረብዕ ተደርገዋል፡፡ ዋይዳድ ካዛብላንካ ከዜስኮ ዩናይትድ ጋር ነጥብ ሲጋራ አል አሃሊ ከአሴክ ሚሞሳስ ያለምንም ግብ አቻ ተለያይተዋል፡፡ ከምድብ መውደቁን አስገድሞ ያረጋገጠው ኢኒምባ ማሜሎዲ ሰንዳውንስን 3-1 መርታት ችሏል፡፡

ምድብ አንድን በበላይነት ለመጨረስ ንዶላ ላይ በተደረገው ጨዋታ ዜስኮ ዩናይትድ ከዋይዳድ ካዛብላንካ 1 አቻ ተለያይተዋል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ እና የግብ ሙከራ የበላይነት የነበራቸው ዜስኮዎች በኬንያዊው ኢንተርናሽናል ዴቪድ ኦዌኖ ግብ ቀዳሚ መሆን ችለዋል፡፡ የዋይዳድን የአቻነት ግብ ናይጄሪያዊው ቺሶማ ቺካታራ በድንቅ ሁኔታ ከመረብ አሳርፏል፡፡ በቻን 2016 ለናይጄሪያ የተሻለ እንቅስቃሴ ያሳየው የቀድሞ የአቢያ ዋርየርስ አጥቂ ቺካታራ ለዋይዳድ በመጀመሪያው የነጥብ ጨዋታ ነው ግብ ማስቆጠር የቻለው፡፡ የአቻ ውጤቱ በዌልሳዊው ጆን ቱሻክ የሚመራውን የሞሮኮ ክለብ ምድቡን በበላይነት እንዲያጠናቅቅ ረድቶታል፡፡

በምድቡ በተደረገ ሌላ ጨዋታ አቢጃን ላይ አሴክ ሚሎሳስ ከአል አሃሊ 0-0 ጨዋታቸውን ጨርሰዋል፡፡ ጨዋታው ከመርሃ ግብር ሟሟያነት በተረፈ ትርጉም ያልነበረው ሲሆን ብዙም ማራኪ እንቅስቃሴ ያልታየበት ሁኖ አልፏል፡፡

ኢኒምባ በስተመጨረሻም ማሸነፍ ችሏል፡፡ ፖርት ሃርትኮርት ላይ በተደረገው ጨዋታ የደቡብ አፍሪካው ቻምፒዮን ማሜሎዲ ሰንዳውን በምድብ ጨዋታው የመጀመሪያ ሽንፈትን ቀምሷል፡፡ ጆን ኡቼ ኢኒምባን ቀዳሚ ሲያደርግ ፐርሲ ታኦ ብራዚሎቹን አቻ ማድረግ ችሏል፡፡ የሞፎን ኦዶ ሁለት ግቦች ዳግም ኢኒምባን ወደ መሪነት መልሷል፡፡ ምድቡን ማሜሎዲ ሰንዳውንስ በ9 ነጥብ መሪ ሆኖ ሲያጠናቅቅ እና ዛማሌክ በሁለተኝነት ጨርሷል፡፡

በግማሽ ፍፃሜ ዋይዳድ ካዛብላንካ ከዛማሌክ በሰሜን አፍሪካ ደርቢ ሲገናኙ ማሜሎዲ ሰንዳውን ዜስኮ ዩናይትድን የሚገጥም ይሆናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *