ኮንፌድሬሽን ካፕ፡ ኤምኦ ቤጃያ ግማሽ ፍፃሜውን ተቀላቅሏል

የ2016 ኦሬንጅ ካፍ ኮንፌድሬሽን ካፕ የምድብ ጨዋታዎች ማክሰኞ እና ዕረቡ በተደረጉ ጨዋታዎች ተጠናቅቀዋል፡፡ ሶስቱ የግማሽ ፍፃሜ ተፋላሚዎች አስቀድመው በመታወቃቸው በምድብ አንድ ኤምኦ ቤጃያ እና ሚዲአማን ያገናኘው ጨዋታ ወሳኝ ነበር፡፡ ቲፒ ማዜምቤ ያንግ አፍሪካንስ 3-1 ሲረታ የምድብ ሁለትን የበላይነት ለመያዝ ራባት ላይ የተፋጠጡት ፉስ ራባት እና ኤቷል ደ ሳህል ጨዋታቸውን በአቻ ውጤት ጨርሰዋል፡፡ ካውካብ ማራካሽ ከአል አሃሊ ትሪፖሊ 2-2 ተለያይተዋል፡፡

በአጣብቂኝ ውስጥ የነበረው ኤምኦ ቤጃያ ሚዲአማን 1-0 በመርታት ወደ ግመሽ ፍፃሜ ማለፉን አረጋግጧል፡፡ ሚዲአማ ከጨዋታው በፊት የማለፍ የተሻለ ዕድል የነበረው ቢሆን ከኮንፌድሬሽኑ ምድን ከመሰናበት አልዳነም፡፡ ትውልደ ፈረንሳይ ቻዳዊው ሞርጋን ቤቶራንጋል የቤጃያን የማሸነፊያ ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡ ቤጃያ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ሲቀላቀል ያስቆጠረው የግብ መጠን ሁለት ብቻ መሆኑ ብዙዎችን አስገርሟል፡፡

ሉቡምባሺ ላይ ያንግ አፍሪካንስን ያስተናገደው ቲፒ ማዜምቤ 3-1 ማሸነፍ ችሏል፡፡ የጨዋታ የበላይነት የነበራቸው ማዜምቤዎች በጆናታን ቦሊንጊ እና ሬንፎርድ ካላባ (2) ግቦች ማሸነፍ ችሏል፡፡ ቪንሰት ቺኩፒ በቀይ ካርድ መውጣቱን ተከትሎ በ10 ተጫዋች የተጫወቱት ያንጋዎች በብሩዳዊው አሚሲ ታምብዌ የማስተዛዘኛ ግብ ማግኘት ችሏል፡፡

ፉስ ራባት የምድብ ሁለት የበላይቱን አስጠብቆ መውጣት በቻለበት ጨዋታ ከቱኒዚያው ቻምፒዮን ኤቷል ደ ሳህል ጋር ያለምንም ግብ አቻ ተለያይተዋል፡፡ ውጤቱ የሞሮኮ ቻምፒዮኑን የምድብ የበላይነቱን እንደያዘ ወደ ግማሽ ፍፃሜውን እንዲቀላቀል አስችሏል፡፡

ካውካብ ማራካሽ እና አል አሃሊ ትሪፖሊ የምድብ መጨረሻ ጨዋታቸውን በአቻ ውጤት አጠናቅቀዋል፡፡ ካውካብ በአብደሊላ አሚሚ ግብ ቀዳሚ ሲሆን  ፉአድ መሃመድ በፍፁም ቅጣት ምት የሊቢያውን ክለብ አቻ አድርጓል፡፡ እንግዶቹ በመሃመድ ሳሊህ አሊ ግብ መሪነቱን በሁለተኛው አጋማሽ ቢጨብጡም አህመድ ቻጉ በፍፁም ቅጣት ምት የሞሮኮውን ክለብ አቻ አድርጓል፡፡

በግማሽ ፍፃሜው ቲፒ ማዜምቤ ከኤቷል ደ ሳህል ሲገናኙ በሰሜን አፍሪካ ደርቢ ፉስ ራባት ከኤምኦ ቤጃያ ለፍፃሜ ለማለፍ ይፋለማሉ፡፡

Leave a Reply