ጋቦን 2017፡ ሚቾ ኮሞሮስን በሚገጥመው ስብስባቸው አይዛክ ኢዜንዴን ሲያካተቱ ኦዶንካራን ዘለውታል

የቅዱስ ጊዮርጊሱ ግብ ጠባቂ ሮበርት ኦዶንካራ ሃገሩ ዩጋንዳ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከኮሞሮስ ላለባት ጨዋታ ከብሄራዊ ቡድኑ ውጪ ሆኗል፡፡

ከ2010 ጀምሮ የክሬንሶቹ ሁለተኛ ግብ ጠባቂ የነበረው ኦዶንካራ ከሰርቢያዊው ሚሉቲን ‘ሚቾ’ ሰርዪቪች የ32 ተጫዋቾች ስብስብ ሳይካተት ቀርቷል፡፡

የአምስት ግዜ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኮከብ ግብ ጠባቂው ኦዶንካራ ክለብ ጊዮርጊስ በኢትዮጵያ የሊግ ዋንጫ ሶስት ጨዋታዎች በጉዳት ያመለጠው ሲሆን ከዩጋንዳ ብሄራዊ ቡድን ለመቀነሱ ግን እንደምክንያትነት አልቀረበም፡፡ በኦዶንካራ ከቡድኑ ያለመካተት ዙሪያ ሚቾ ለሶከር ኢትዮጵያ ከካምፓላ በሰጡት አስተያየት ኦዶንካራ ከእንቅስቃሴ በመራቁ እንዳልመረጡች ተናግረዋል፡፡

“ሮበርት የቅድመ ውድድር ዘመን ባለመጀመሩ ልምምድ በማድረግ ላይ አይገኝም፡፡ ከሱ በተለየ ሌሎች ግብ ጠባቂዎች ደግሞ በጨዋታ እና ልምምድ ላይ በመገኘታቸውን ቅድሚያውን ለነሱ ሰጥቻለው፡፡” ብለዋል፡፡

ሌላው የፈረሰኞቹ የመሃል ተከላካይ አይዛክ ኢዜንዴ በቡድኑ ውስጥ መካተት ችሏል፡፡ ኢዜንዴ ለዕረፍት ዩጋንዳ በተገኘበት ወቅት አቋሙን ለመጠበቅ የዩጋንዳ አዛም ፕሪምየር ሊግ ክለብ ሳዶሊን ፔንትስ የቅድመ ውድድር ዘመን ጨዋታዎች መካፈል ችሏል፡፡

ሚቾ በቡድኑ ውስጥ የማሜሎዲ ሰንዳውንስ ግብ ጠባቂ ዴኒስ ኦኒያንጎን፣ የኤል ሜሪኩን ጀማል ሳሊምን እና የ2015 የሴካፋ ዋንጫ ኮከብ ግብ ጠባቂ ኢስማኤል ዋቴንጋን አካተዋል፡፡ የዩጋንዳ አዛም ፕሪምየር ሊግ ኮከብ ተጫዋች ጆሴፍ ኦቻያ፣ ፋሩክ ሚያ እና ካሊድ ኦቾ በቡድኑ ውስጥ የተካተቱ ሌሎች ተጫዋቾች ናቸው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *