ሽመልስ በቀለ የፔትሮጄት ውሉን አራዝሟል

የዋሊያዎቹ የአጥቂ አማካይ ሽመልስ በቀለ በስዌዙ ክለብ ፔትሮጀት ያለው ቆይታ በሁለት አመት ማራዘሙን ተነግሯል፡፡

የተጫዋቹ ግብፃዊ ወኪል አብዱልራህማን መግዲ የሽመልስን ውል መራዘም በግል የኢንስተግራም ገፁ ላይ አስፍሯል፡፡

በመጀመሪያው የግብፅ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ዘሙ ድንቅ ብቃቱን ያሳየው የቀድሞ የሃዋሳ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ አማካይ ሽመልስ በ2015/16 የውድድር ዘመን ስድስት ግቦችን ሲያስቆጥር አንድ ግብ የሆነ ኳስ አመቻችቶ ማቀበል ችሏል፡፡

ሽመልስ በዓመቱ አጋማሽ ከፔትሮጀት መልቀቅ ማሰቡን ለሶከር ኢትዮጵያ መግለፁ ቢታወስም ወደ ቋሚ አሰላለፉ ዳግም መመለሱ እና በጥሩ ብቃት የውድድር ዘመኑን መጨረሱ የሃሳብ ለውጥ እንዲኖር ያስቻለው ይመስላል፡፡

ሽመልስ የሱዳኑን ኤል ሜሪክ ለቆ ፔትሮጀትን ከተቀላቀለ በኃላ ከሞላ ጎደል ስኬታማ ግዜያትን ማሳለፍ ችሏል፡፡ ተጫዋቹ በግብፅ ፕሪምየር ሊግ ሃት-ትሪክ የሰራ ብቸኛው ኢትዮጵያ ሲሆን በሊቢያ እና ሱዳን የተሳካ የእግርኳስን ህይወትን መምራት ችሏል፡፡

ሽመልስ ከአዲሱ ሚሌንየም ወዲህ በኢትዮጵያ ከታዩ ድንቅ አማካዮች መካከል አንዱ ሲሆን የአጫዋወት መንገዱ በብዙ ግብፃዊያን ተወዳጅ እንዲሆን አስችሎታል፡፡

የሽመልስ መፈረምን ተከትሎ ሎሌላኛው ኢትዮጵያዊ አጥቂ ኡመድ ኡኩሪ ወደ ፔትሮጀት ለመዛወር ድርድር ላይ እንደሚገኝ ሶከር ኢትዮጵያ ከግብፅ ባገኘችው መረጃ ማወቅ ችላለች፡፡

 

Leave a Reply