ኡመድ ኡኩሪ ለግብፁ ኤንታግ ኤል ሃርቢ ፈርሟል

የቀድሞ የመከላከያ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የፊት መስመር ተሰላፊ ኡመድ ኡኩሪ ለግብፅ ፕሪምየር ሊጉ ክለብ ኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢ ፊርማውን አኑሯል፡፡ 

ኡመድ ከኢኤንፒፒአይ ጋር የነበረውን ውል በስምምነት ያፈረሰ ሲሆን በሁለት ዓመት ውስጥ ወደ ሶስተኛው ክለብ ማምራት ችሏል፡፡

ኡመድ በዓመቱ መጀመሪያ ወደ ነዳጅ አምራቾቹ ኢኤንፒፒአይ በአራት ዓመት ውል ቢያመራም በቂ የመሰል ዕድል መነፈጉ ከክለቡ የመውጫ በር እንዲፈልግ አስገድዶታል፡፡

ኡመድ በኢኤንፒፒአይ ቆይታው የኮትዲቯሩ አፍሪካን ስፖርትስ ላይ በካፍ ኮንፌድሬሽን ካፕ ግብ ማስቆጠር የቻለ ሲሆን በ2015/16 የውድድር ዘመን በሊግ ጨዋታ ግብ ማስቆጠር አልቻለም ነበር፡፡

የ2006 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኮከብ ግብ አግቢ የሆነው ኡመድ ለኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢ የአንድ ዓመት ውል መፈረሙን የተጫዋቹ ወኪል አብዱልራህማል መግዲ ገልጿል፡፡ ግብፃዊው መግዲ ከኡመድ ባሻገር የሽመልስ በቀለ ወኪል ነው፡፡

በ2004 እ.ኤ.አ. የተመሰረተው ኤል ሃርቢ የካይሮ ክለብ ሲሆን ባሳለፍነው የውድድር ዘመን በግብፅ ፕሪምየር ሊግ ሰባተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቅቋል፡፡ ክለቡ በቀድሞ የግብፅ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሻውኪ ጋሪብ የሚመራ ነው፡፡ ጋሪብ ከ2004-2011 የሃሰን ሸአታ ምክትል በመሆን ፈርኦኖቹን ያገለገሉ ሲሆን ከ2013-14 ለአንድ ዓመት ቦብ ብራድሊን ተክተው የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ነበሩ፡፡ 30ሺ ተመልካች የመያዝ አቅም ባለው አል ሰለም ስታዲየም የሜዳ ላይ ጨዋታዎቹን የሚያደርገው ክለቡ በግብፅ ጦር ሚኒስቴር ስር የሚተዳደር ክለብ ነው፡፡

ኡመድ በግብፅ ቆይታው ለኢትሃድ አልክሳንደሪያ እና ኢኤንፒፒአይ መጫወት ችሏል፡፡

Leave a Reply