“በአዲሱ ክለቤ ጥሩ የውድድር ዘመን እንደማሳልፍ ተስፋ አደርጋለሁ” ኡመድ ኡኩሪ

ኢትዮጵያዊው አጥቂ ኡመድ ኡኩሪ ባሳለፍነው ቅዳሜ የግብፁ ኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢን በነፃ ዝውውር ተቀላቅሏል፡፡ ኡመድ ለካይሮው ክለብ የአንድ ዓመት ውል የፈረመ ሲሆን የቅድመ ውድድር ዝግጅትም ከክለቡ ጋር በቅርቡ በመቀላቀል እንደሚጀምር ታውቋል፡፡

ኡመድ ከዝውውሩ መጠናቀቅ በኃላ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠው አስተያየት ከኢኤንፒፒአይ የነበረውን ቀሪ የሶስት ዓመት ውል በስምምነት ማፍረሱን ገልጿል፡፡“ኢኤንፒፒአዮች በነፃ ሊለቁኝ አልፈለጉም ነበር፡፡ ምክንያቱም ዓምና ስፈርም ብዙ ብር ስላወጡብኝ በቀላሉ ሊለቁኝ ፍቃደኛ አልነበሩም፡፡ እኔ ደግሞ በኢኤንፒፒአይ የመቀጠል ምንም ዓይነት ፍላጎት አልነበረኝም፡፡ በዓመት ውስጥ ጥቂት ጨዋታ ማድረጌ ደስተኛ ስላላደረገኝ ወደ ሌላ ክለብ መዛወር እንዳለብኝ አስብ ነበር፡፡ ኢኤንፒፒአይ በውሰት ለሌላ ክለብ ሊሰጠኝ ያስብ ነበር ነገርግን እኔ ከክለቡ መለየትን የመጀመሪያ ምርጫዬ አድርጊያለው፡፡” ይላል የቀድሞ የመከላከያ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የፊት መስመር ተሰላፊ፡፡

ኡመድ በግብፅ ከሚገኙ ክለቦች በተጨማሪም ስማቸው ያልተጠቀሰ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ክለቦች (በተለይ የዱባይ ክለቦች) ፊርማውን ለማግኘት ሲጥሩ ነበር፡፡ ኡመድ በፔትሮጀት ተፈልጎ የነበረ ቢሆንም በውል ስምምነት ምክንያት ወደ ስዌዙ ክለብ ሳያቀና ቀርቷል፡፡ “ፔትሮጀት የሊግ ጨዋታ ከመጠናቀቁ ከአራት ጨዋታዎች በፊት ነው ለዝውውር የጠየቁኝ፡፡ እኔም ተስማምቼ ነበር ምክንያቱም ጓደኛዬ ሽመልስ በቀለ እዛው ስለሚጫወት ከሱ ጋር በጥሩ መልኩ መቀናጀት ስለምንችል እና አሰልጣኙ (ታላት የሱፍ) ጋር ስለምንግባባ ነበር፡፡ ቢሆንም ፔትሮጀት ያቀረበልኝ የሶስት ዓመት ውል ነበር፡፡ እኔ ደግሞ ረጅም ግዜ ውል በኢትሃድ አሌክስአንድሪያ እና ኢኤንፒፒአይ ፈርሜ የተፈጠረው ነገር ጥሩ ስላለሆነ የአንድ ዓመት ውል እንዲያቀርቡልኝ ወኪሌ አነጋግሯቸው ነበር፡፡ በውል ስምምነት ላይ ሳንስማማ ቀረን፡፡” ይላል፡፡

በኡመድ ፍላጎት መሰረት የአንድ ዓመት ውል ያቀረበው ኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢ የኡመድ ቀጣይ ማረፊያ ሆኗል፡፡ “ክለቡ የአንድ ዓመት ውል ስላቀረበልኝ ልፈርም ችያለው፡፡ ካልተመቸህ ለአንድ ዓመት ብቻ ስለሆነ ከክለቡ ለመለያየትም ጥሩ መንገድ ነው፡፡ ክለቡ ዓመና 7ኛ ሆኖ ነው የጨረሰው፡፡ ብዙ ስኒየር ተጫዋቾችን የያዘ ክለብ ነው፡፡ በብዛት ዕድሜያቸው ከሰላሳ በላይ የሆናቸውን ተጫዋቾች የያዘ ክለብ ነው፡፡ ከኢኤንፒፒአይ ጋር በአጨዋወት መንገዳቸው ልዩነት አላቸው፡፡ ኢኤንፒፒአይ በብዛት የዓየር ላይ ኳስን ይጠቀማል ፤ ኤል ሃርቢ ደግሞ ኳስን መስርቶ የሚጫወት ቡድን ነው፡፡”

ኡመድ ከታዋቂው ግብፃዊ አሰልጣኝ ሻውኪ ጋሪብ ጋር የተገናኘ ሲሆን ከአሰልጣኙ ጋር ጥሩ የውድድር ዘመን እንደሚያሳልፍም ተስፋ እንዳለው ተናግሯል፡፡ “አሰልጣኙ በኔ ዕምነት አለው፡፡ በኢኤንፒፒአይ የተፈጠረውን ነገር በደንብ ያውቃል፡፡ እሱም የነገረኝ ይህንን ነው፡፡ ደስ የሚል አሰልጣኝ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ ሲያነጋግር ዕርጋታ አለው፡፡ ካጋጠሙኝ የግብፅ አሰልጣኞች ጋር ሰፊ የሆነ ልዩነት አለው፡፡ ብዙዎቹ እየጮሁ ተጫዋችን ያደናብራሉ ሻውኪ ከነዚህ የተለየ ነው፡፡ ከሱ ጋር ጥሩ ግዜ እንደማሳልፍ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡”

በቂ የጨዋታ ግዜን አሁን ላይ በተሻ ለ ሁኔታ እንደሚያገኝ የሚጠበቀው ኡመድ ከክለቡ ጋር በቅርቡ የቅድመ ውድድር ዝግጅትን የሚቀላቀል ይሆናል፡፡ ተጫዋቹ በኢትዮጵያ ለአንድ ወር ያህል በዕረፍት ያሳለፈ ሲሆን ከዝውውሩ መጠናቀቅ በኃላ ያልተቆጩ ጉዳዩችን ከጨረሰ በኃላ ወደ ቅድመ ውድድር ዝግጅት እንደሚመራ ይናገራል፡፡ “ክለቡ ዝግጅት በዱባይ ጀምሯል፡፡ አንዳንድ መጨረስ ያለብኝን ጉዳዮች ከጨረስኩ በኃላ ክለቡን ለዝግጅት እቀላቀላለው፡፡ በአዲሱ ክለቤ ጥሩ የውድድር ዘመን እንደማሳልፍ ተስፋ አለኝ፡፡ የመሰለፍ ዕድልም ስለማገኘ ዳግም ወደ ብሄራዊ ቡድኑ የማልጠራበት ምክንያት አይኖርም፡፡” ሲል ሃሳቡን አጠናቅቋል፡፡

Leave a Reply