ከ17 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን ለማሊው ጨዋታ ዝግጅቱን ነገ ይጀምሯል

በማዳጋስካር አስተናጋጅነት ለሚካሄደው ለሚካሄደው የአፍሪካ ከ17 አመት በታች ዋንጫ ግብጽን በድምር ውጤት 5-2 በመርታት ወደ ተከታዩ የማጣርያ ዙር ያለፈው የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን ከአንድ ሳምንት እረፍት በኋላ ለቀጣዩ ጨዋታ ዝግጅት ተሰባስበዋል፡፡

ቀይ ቀበሮዎቹ በአፋረንሲስ ሆቴል መቀመጫቸውን ያደረጉ ሲሆን ለቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት በአዲስ አበባ ልምምድ እያደረጉ ቆይተው ወደ ሀዋሳ እንደሚያቀኑ ታውቋል፡፡

አሰልጣኝ አጥናፉ ከስብስባቸው የሚቀነስ ተጫዋች እንደሌለ ያስታወቁ ሲሆን ቡድኑን ይበልጥ ለማጠናከር በሀዋሳ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ከሚገኘው ከ17 አመት በታች የክልል ፕሮጀክቶች የምዘና ውድድር ላይ በመገኘት ምልመላ እያደረጉ መሆኑን ለማወቅ ችለናል፡፡

ከ17 አመት በታች ቡድኑ ከማሊው ጨዋታ በፊት ከሱዳን አቻው ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ሀዋሳ ላይ ለማድረግ ጥረት በማድረግ ላይ ሲገኝ የኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በገባላቸው ቃል መሰረት በቀጣዮቹ ቀናት የማበረታቻ ሽልማት የሚሰጣቸው ይሆናል፡፡

በኢትዮጵያ እና ማሊ መካከል የሚደረገው የመጨረሻው ዙር የአፍሪካ ከ17 አመት በታች ዋንጫ ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታ ማሊ ባማኮ ላይ ሲደረግ የመልሱ ጨዋታ በሀዋሳ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

1 Comment

Leave a Reply