የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ከጣልያኑ ግዙፍ የትጥቅ አምራች ኤሪያ ጋር የትጥቅ አቅርቦት ውል ተፈራርሟል፡፡ ስምምነቱ ከ1 ወር በፊት ቢፈፀምም ይፋ የተደረገው ዛሬ ነው፡፡
ኤሪያ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሄራዊ ቡድኖች እንደየደረጃቸው የትጥቅ አቅርቦት ለ4 ዓመት ለማቅረብ ሲስማማ ውሉ ግን በሁለቱ ወገኖች ስምምነት በየአመቱ እንደሚታደስ ዛሬ ከቀኑ 10፡00 በጣሊያን ባህል ማዕከል በተሰጠ መግለጫ ተገልጿል፡፡
የትጥቅ አቅራቢው ድርጅት ከፍተኛ አመራሮች ምርታቸውን በኢትዮጵያ የማስተዋወቅ አላማ እንዳላቸው በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተገልጿል፡፡ “የድርጅታችንን ምርቶች በከፍተኛ ሁኔታ በኢትዮጵያ ለማስተዋወቅ እንፈልጋለን፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የእግር ኳስ እምቅ አቅም ለማውጣት የበኩላችንን ጥረት እናደረጋለን፡፡
“እዚህ መጥተን መስራታችን ደስተኛ አድርጎናል፡፡ አፍሪካ ውስጥ መስራት ከጀመርን ትንሽ ቆየት ብለናል ፤ በተለይ በጋቦን ለሊጎቹ ክለቦች የትጥቅ አቅርቦቶችን እናቀርባለን፡፡ ከዚህ በኃላ ደግሞ ከስፖርት ኮሚሽኑ ጋር በመነጋገር አብዛኞቹን የስፖርት አይነቶች ለመያዝ እንሞክራለን፡፡ ” ሲሉ የተናገሩት ሚስተር ሮቤርቶ በቀጣይ ስላላቸው እቅድም እንደሚከተለው ተናግረዋል፡፡
” በቀጣይ በተለይ የፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ ለሆኑ ሃገራት ትጥቆችን ለማቅረብ ድርድሮችን እያደረግን ነው፡፡ይህ ደግሞ አድማሳችንን ለማስፋት እና ምርታችንን በሰፊው ለአፍሪካ ሃገራት ለማስተዋወቅ ይረዳናል”ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ጁነይዲ ባሻ በበኩላቸው በውሉ እንደተደሰቱ ገልጸዋል፡፡
“እስከ ዛሬ ድረስ ለብሄራዊ ቡድኖቻችን የትጥቅ አቅርቦት የሚያቀርብልንን ድርጅት ስንጠብቅ ነበር፡፡ አሁን ግን ጥራት ያላቸውን ምርቶች የሚያቀርብልንን ድርጅት ማግኘታችን እጅግ አስደስቶናል፡፡
“ስለ ማሊያው ዲዛይን በተቻለን አቅም የማሊያዎቹን ዲዛይን ከራሳችን ባህል ጋር ለማመሳሰል እና እኛን እንዲገልፀን ለማድረግ እንሞክራለን፡፡ አሁን ለቅዳሜው ጨዋታ እንዲደርስልን ብለን ተሯሩጠን የተሻለ ነገር እንዲሰራ አድርገናል፡፡ ነገር ግን ዲዛይኑን በቀጣይ ለማሻሻል ከወዲሁ ጥረት እያደረግን ነው” ብለዋል፡፡
ኤሪያ የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያ በአለም ደረጃ ተቀባይነት ያገኘ ድርጅት ሲሆን ከዚህ በፊት ለጣልያኑ ፓርማ ለእንግሊዙ ኖርዊች ሲቲ ትጥቅ ያቀረበ ሲሆን በ2016 የአውሮፓ ዋንጫ ላይ ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረገው የአይስ ላንድ ብሄራዊ ቡድን ትጥቆችን ያቀረበ ድርጅት ነው፡፡
ድርጅቱ ለብሄራዊ ቡድኖቻችን ሶስት የተለያዩ ማሊያዎች እና ቱታዎችን እንዲሁም የእረፍት ልብሶችን በየአመቱ እንደሚያቀርብ ተገልጿል፡፡ ስምምነቱ በየአመቱ ሲታደስ ብሄራዊ ቡድኖቻችን ውጤት ባመጡ ቁጥር ውሉ ላይ ማሻሻያ እንደሚደረግ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተነግረዋል፡፡