በ12ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ሲዳማ ቡና ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ወላይታ ድቻ ተጋጣሚዎቻቸውን በማሸነፍ የደረጃ ሰንጠረዡን አናት ሲቆጣጠሩ ኢትዮጵያ ቡና ከይርጋለም በሽንፈት ተመልሷል፡፡

ቅዳሜ በአበበ ቢቂላ በተደረጉ ጨዋታዎች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መከላከያን 3-1 ሲረታ አርባምንጭ ከነማን ያስተናገደው ደደቢት አቻ ተለያያቷል፡፡ ንግድ ባንክ መከላከያን 3-1 በረታበት ጨዋታ ሰለሞን ገብረመድህን ፣ ፊሊፕ ዳውዚ እና ኤፍሬም አሻሞ ለባንክ ሲያስቆጥሩ ሙሉአለም ጥለሁን የመከላከያን ግብ አስቆጥሯል፡፡ ቀጥሎ በተካሄደው የደደቢት እና አርባምንጭ ጨዋታ ሰማያዊው ጦር እስከ ጨዋታው መገባደጃ ድረስ ሳሚ ሳኑሚ ባስቀጠረው ግብ መምራት ቢችልም በረከት ገ/ፃዲቅ በ92ኛው ደቂቃ ከመረብ ያሳረፋት ግብ አርባምንጭን ነጥብ ተጋርተው እንዲወጡ አስችላለች፡፡

ሊጉ እሁድ በክልል ከተሞች ሲቀጥል ወደ ወልድያ የተጓዘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ወልድያን 3-0 አሸነንፎ ተመልሷል፡፡ የቀዱስ ጊዮርጊስን ድል ግቦች ፍፁም ገብረማርያም (2) እና አሉላ ግርማ ከመረብ አሳርፈዋል፡፡

ቦዲቲ ላይ ሙገር ሲሚንቶን ያስተናገደው ወላይታ ድቻ በአላዛር ፋሲካ ብቸኛ ግብ 1-0 በሆነ ውጤት አሸንፎ 3ኛ ደረጃን ከኢትዮጵያ ቡና ተረክቧል፡፡

ይርጋለም ላይ ኢትዮጵያ ቡነን ያስተናገደው መሪው ሲዳማ ቡና 1-0 አሸንፎ መሪነቱን አስጠብቋል፡፡ የሲዳማ ቡናን የድል ግብ ያስቆጠረው ኬንያዊው አጥቂ ኤሪክ ሙራንዳ ነው፡፡

አዳማ ላይ አዳማ ከነማ ዳሽን ቢራን 1-0 አሸንፎ ደረጃውን ወደ 5ኛነት ከፍ አድርጓል፡፡ የአዳማን የድል ግብ ከመረብ ያሳረፈው ወንድወሰን ቦጋለ ነው፡፡

ሀዋሳ ላይ አሰልጣኙ ታረቀኝ አሰፋን አሰናብቶ በጊዜያዊ አሰልጣኙ አዲሱ ካሳ እየተመራ ያለው ሀዋሳ ከነማ ኤሌክትሪክን አስተናግዶ በአዲስ አለም ተስፋዬ አና ተመስገን ተክሌ ግቦች 2-1 አሸንፈዋል፡፡

ሊጉን ሲዳማ ቡና በ26 ነጥቦች ሲመራ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እርስ በእርስ የሚያደርጉት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ወላይታ ድቻ በ21 እና 20 ነጥቦች ይከተላሉ፡፡

ያጋሩ