በሁለት ምድቦች ተከፍሎ በ32 ቡድኖች መካከል ሲካሄድ የቆየው የ2008 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ዛሬ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በደማቅ ሁኔታ ተጠናቋል፡፡
ከቀኑ 7፡00 በተደረገው የደረጃ ጨዋታ ወልድያ ከ አዲስ አበባ ከተማ መደበኛውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 1-1 በሆነ ውጤት አጠናቀዋል፡፡ ኃይሌ እሸቱ አዲስ አበባ ከተማን ቀዳሚ ሲያደርግ ያሬድ ሀሰን ወልድያን አቻ አድርጓል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች ለእረፍት እንደወጡ የጣለው ከባድ በረዶ አዘል ዝናብ ጨዋታውን ለ40 ደቂቃዎች ያክል እንዲገፋ አድርጎታል፡፡ ጨዋታው በመደበኛው ክፍለ ጊዜ አቻ መጠናቀቁን ተከትሎ አሸናፊውን ለመለየት በተሰጡት የመለያ ምቶች አዲስ አበባ ከተማ 8-7 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ሶስተኛ ሆኖ አጠናቋል፡፡
ቀጥሎ በተከናወነው የፍፃሜ ጨዋታ ፋሲል ከተማ ጅማ አባ ቡናን ከፍፁም የጨዋታ ብልጫ ጋር 3-1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የ2008 የከፍተኛ ሊጉ አሸናፊ ሆኖ አጠናቋል፡፡
ሄኖክ ገምቴሳ ፣ አብዱልራህማን ሙባረክ እና አቡበከር ደሳለኝ የፋሲልን የድል ግቦች ሲያስቆጥሩ አሜ መሃመድ የጅማ አባቡናን ብቸኛ ግብ አስቆጥሯል፡፡
የጨዋታውን ፍጻሜ ተከትሎ የሽልማት ስነስርአት ፕሮግራም የቀጠለ ሲሆን ተሸላሚዎች እንደሚከተለው ሆነዋል፡፡
ኮከብ ዋና ዳኛ
ኢብራሂም ነጋሽ – ዋንጫ እና 7000 ብር
ኮከብ ረዳት ዳኛ
ተስፋዬ በየነ – ዋንጫ እና 6000 ብር
ከፍተኛ ግብ አግቢ
አሜ መሃመድ (21 ግቦች) – ዋንጫ እና 12,000 ብር
ኮከብ ተጫዋች
አብዱልራህማን ሙባረክ (ፋሲል ከተማ) – 12,000
ኮከብ ግብ ጠባቂ
ተክለማርያም ሻንቆ (አአ ከተማ) – ዋንጫ እና 12,000 ብር (አምና የብሄራዊ ሊግ ኮከብ ግብ ጠባቂ ተብሎ መመረጡ ይታወሳል፡፡
ኮከብ አሰልጣኝ
ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ (ፋሲል ከተማ) – 12,000 ብር እና ዋንጫ
የስፖርታዊ ጨዋነት ዋንጫ
ኢት.ውሃ ስራ (ምድብ ሀ) እና አአ ከተማ (ምድብ ለ)
የምድባቸው አሸናፊዎች
ጅማ አባቡና እና ፋሲል ከተማ የዋንጫ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡
የደረጃ ሽልማቶች
3ኛ. አአ ከተማ – የነሀስ ሜዳሊያ እና 40,000 ብር
2ኛ. ጅማ አባቡና – የብር ሜዳሊያ እና 50,000 ብር
3. ፋሲል ከተማ – ዋንጫ ፣ የወርቅ ሜዳሊያ እና 60,000 ብር