የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከሲሸልስ ጋር ለሚያደርገው ጨዋታ ዝግጅቱን ቀጥሏል፡፡ ዋሊድ አታም ብሄራዊ ቡድኑን ትላንት ተቀላቅሏል፡፡
ዛሬ 10:00 ላይ በነበረው ልምምድ ላይ በሲሸልሱ ጨዋታ ላይ ቋሚ ተሰላፊ የሚሆኑ ተጫዋቾችን ፍንጭ በሚሰጥ መልኩ ለሁለት ተከፍለው ተጫውተዋል፡፡ በዛሬው ልምምድ ላይ ትላንት ቡድኑን የተቀላቀለው ዋሊድ የተገኘ ሲሆን አቤል ማሞ እና እንዳለ ከበደ በልምምዱ ላይ አልተሳተፉም፡፡ አህመድ ረሺድ መጠነኛ ጉዳት አጋጥሞት ልምምዱን አቋርጦ የወጣ ሲሆን ሌሎቹ ተጨዋቾች በሙሉ ጤንነት ላይ ይገኛሉ፡፡
የሲሸልስ ብሄራዊ ቡድን 19 የቡድን አባላትን ይዞ ዛሬ ምሽት አዲስ አበባ የሚገባ ሲሆን የተቀረው የልኡካን ቡድን ነገ አመሻሽ ላይ የሚገባ መሆኑ ለጨዋታው የሰጠው ግምት አነስተኛ መሆኑን ያሳያል፡፡
ጨዋታው ቅዳሜ በአዲሱ የሀዋሳ ኢንተርናሽናል ስታድየም የሚካሄድ ሲሆን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከጣልያኑ ኤሪያ ጋር በገባው ውል መሰረት ዋልያዎቹ ለመጀመርያ ጊዜ የኤሪያ ምርቶችን ለብሰው ወደ ሜዳ ይገባሉ፡፡