በ11ኛው ሳምንት ሲዳማ ቡና መሪነቱን ሲያጠናክር ኢትዮጵያ ቡና ወደ አሸናፊነት ተመለሰ

በ11ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ሲዳማ ቡና መሪነቱን ሲያጠናክር ኢትዮጵያ ቡና እና ወላይታ ድቻ ደረጃቸውን አሻሽለዋል፡፡

ቅዳሜ በተደረጉ ሁለት የአበበ ቢቂላ ስታድየም ጨዋታዎች እንግዳዎቹ ቡድኖች ድል ቀንቷቸው ተመልሰዋል፡፡ በ8 ሰአት ወላይታ ድቻን ያስተናገደው ንግድ ባንክ 1-0 በሆነ ውጤት ተሸንፏል፡፡ የድቻን የማሸነፍያ ግብ ያስቆጠረው ባየ ገዛኸኝ በ8ኛው ደቂቃ ነው፡፡ ድሉን ተከትሎ ድቻ በ17 ነጥብ ደረጃውን ወደ 4ኛነት አሻሽሏል፡፡

በ10 ሰአት አዳማ ከነማን ያስተናገደው ኤሌክትሪክ በተመሳሳይ 1-0 ተሸንፏል፡፡ የአዳማ ከነማን የድል ግብ ተቀይሮ የገባው ቢንያም አየለ ከመረብ አሳርፏል፡፡ ለኤሌክትሪክ ይህ ጨዋታ ሶስተኛ ተከታታይ ሽንፈት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

እሁድ ክልል ላይ በተደረጉ ጨዋታዎች ይርጋለም ላይ መሪው ሲዳማ ቡና የመጨረሻ ደረጃ የያዘው ወልድያን 1-0 በማሸነፍ መሪነቱን አጠናክሯል፡፡ ወደ አርባምንጭ የተጓዘው ቅዱስ ጊዮርጊስ በአርባምንጭ ከነማ 1-0 ተሸንፎ ተመልሷል፡፡ የአርባምንጭን የድል ግብ በረከት ደሙ ከመረብ አሳርፏል፡፡

ጎንደር ላይ ዳሽን ቢራ ደደቢትን አስተናግዶ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ጨዋታውን ፈፅሟል፡፡ ደደቢት በ70ኛው ደቂቃ ዳዊት ፍቃዱ ባስቆጠረው ግብ ሲመራ ቢቆይም አስራት መገርሳ በ93ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ግብ የጎንደሩን ክለብ ከሽንፈት ታድጋለቸ፡፡

አሰላ ላይ ሀዋሳ ከነማን ያስተናገደው ሙገር ሲሚንቶ ካለ ግብ 0-0 ሲለያይ አበበ ቢቂላ ለይ በተደረገው የ10 ሰአት ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና መከላከያን 2-0 አሸንፏል፡፡

ሊጉን ሲዳማ ቡና በ23 ነጥብ ሲመራ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና በተመሳሳይ 18 ነጥብ ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል፡፡ የከፍተኛ ግብ አግቢነቱን የኢትዮጵያ ቡናው ቢንያም አሰፋ በ8 ግቦች ይመራል፡፡

ያጋሩ