ኮፓ ኮካ ኮላ፡ ከ15 አመት በታች በሴቶች ፍፃሜ የሚጠበቁ ተጫዋቾች

የኮፓ ኮካኮላ ከ15 አመት በታች የማጠቃለያ ውድድር እሁድ ይጠናቀቃል፡፡ በሴቶች ኦሮሚያ ከ ደቡብ ለዋንጫ የሚጫወቱ ሲሆን በውድድሩ ጥንካሬያቸውን ያሳዩት ሁለቱ ቡድኖች ጠንካራ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ለሁለቱ ቡድኖች ውጤት ማማር ከሚጠቀሱት ተጫዋቾች መካከል የኦሮምያን የተከላካይ መስመር የምትመራው ፌቨን ተስፋዬ እና በግማሽ ፍጻሜው 2 ግቦች አስቆጥራ ደቡብን ወደ ፍጻሜው የመራችው ጤናዬ ላታሞ የሚያደርጉት ፍጥጫም ይጠበቃል፡፡

PicsArt_1472800079053

አዳማ ከተማ ተወልዳ ያደገችው ፌቨን ልዩ ስሙ 04 ተብሎ በሚጠራው ሰፈር ህፃናት መንገድ ላይ እግር ኳስ ሲጫወቱ ተመልክታ እግርኳስን የመጫወት ፍላጎት እንዳደረባት ትናገራለች፡፡ በሂደት ክህሎቷን ያዳበረችው ፌቨን ከአዳማው ሀይልዬ ቁጥር አምስት ትምህርት ቤት ተመርጣ በኮፓ ኮካኮላ ከ15 አመት በታች የማጠቃለያ ውድድር ላይ ኦሮምያን ወክላ ተገኝታለች፡፡

የ8ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ፌቨን የኦሮሚያ ክልል ቡድን ሁለተኛ አምበል ስትሆን ቡድኑን ከኋላ ትመራለች፡፡ እስካሁን በተደረጉት 4 ጨዋታዎች ኦሮምያ ግብ ላለማስተናገዱም ትልቅ ሚና ተጫውታለች፡፡ ” የተጋጣሚን አጥቂዎች ባህርይ በፍጥነት የመረዳት ችሎታ አላት፡፡ ደካማ ጎናቸውን በመጠቀም ያሰቡትን እንዳይተገብሩ ታደርጋለች ” ሲል የቡድኑ አሰልጣኝ ስለ ፌቨን መስክሯል፡፡

የብሄራዊ ቡድኗ አጥቂ ረሂማ ዘርጋን የምታደንቅ ሲሆን ብሄራዊ ቡድኗን በአምበልነት የመምራት ህልም እንዳላት ተናግራለች፡፡

PicsArt_1472799944692

በሲዳማ ዞን ዋና ከተማ ይርጋለም የምትገኘው ትንሽ የገጠር ቀበሌ ማሰንቾ የተገኘችው ጤናዬ ላታሞ የሲዳማ ቡና ሴቶች ቡድን ልምምድ ሲያደርግ ተመልክታ ወደ እግርኳስ የተሳበች ታዳጊ ናት፡፡ ወደ ፊት በከተማዋ ክለብ ሲዳማ ቡና የመጫወት ህልምም አላት፡፡

ይርጋለም ከሚገኘው ትንሳኤ ትምህርት ቤት ለደቡብ ክልል የኮፓ ኮካኮላ ቡድን የተመረጠችው ጤናዬ ወደ ቢሾፍቱ ስትመጣ በዚሁ አካዳሚ እንደምትገባ ተስፋ አድርጋ ነው፡፡ ” ወደ ኀላ መመለስ አልፈልግም” ማለቷንም የቡድኑ አሰልጣኝ ያስታውሳል፡፡

በመጀመርያዎቹ ጨዋታዎች ተጠባባቂ የነበረችው ጤናዬ ራሷን የምታሳይበት እድል ስትፈልግ ቆይታ በግማሽ ፍጻሜው የእሷ ተራ ደረሰ፡፡ አዲስ አበባ ላይ አከታትላ ባስቆጠረቻቸው ሁለት ግቦችም ደቡብን ወደ ፍጻሜው አሻግራለች፡፡

ጤናዬ እና የአጥቂ መስመር አጋሮቿ በፍጻሜው ከጠንካራው የኦሮምያ የተከላካይ መስመር ጋር ይጋፈጣሉ፡፡ ጤናዬ ግን የግማሽ ፍጻሜው ብቃቷን እንደምትደግም ተማምናለች፡፡ ‹‹ ኦሮምያዎች ጠንካራ ተከላካዮች ቢኖራቸውም በችሎታዬ እተማመናለሁ፡፡ ጎልም አስቆጥራለሁ፡፡›› ትላለች፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *