​” የማለፍ ተስፋችን ጠባብ ቢሆንም ተሰላችተን ዝግጅት የምናደርግበት ሁኔታ የለም ” ሽመልስ በቀለ

ኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እና የፔትሮጀቱ አማካይ ዋሊያዎቹን በሃዋሳ ተቀላቅሎ ለመጨረሻው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል፡፡
በግብፅ ቆይታው በውድድር ዘመኑ ስድስት ግቦችን ያስቆጠረው ሽመልስ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ስለብሄራዊ ቡድኑ እና ስለክለቡ ህይወቱ አጠር ያለ ቆይታ አድርጓል፡፡

ቡድኑን ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ነው የተቀላቀልከው ዝግጅት ምን ይመስላል? የማለፍ ተስፋው የጠበበ ነው እና የቡድኑ መንፈስስ እንዴት ነው?

ዝግጅት ጥሩ ነው ምንም አይልም፡፡ ጥሩ ዝግጅት እያደረግን ነው፡፡ ትንሽ የጠበበ እድል ቢኖረንም የቡድኑ መንፈስ ጥሩ ነው፡፡ ሁሉም ተጫዋች ጋር ይህ አስተሳሰብ አይደለም ያለው፡፡ እንደሃገር ስትጫወት ውጤቱን መያዝ ነው ያለብህ እና ወደ አፍሪካው ዋንጫው እንኳን ባታልፍ ውጤቱ ጠቀሜታ አለው፡፡ ተጫዋቾቹ ጋር ያለው የቡድኑ መንፈስ ጥሩ ነው፡፡ እስካሁን ባየሁት ተሰላችተው ልምምድ የሚሰሩበት ሁኔታ የለም፡፡ ጥሩ ዝግጅት ላይ የምንገኘው፡፡”

በጨዋታው ደጋፊው ምን ይጠብቅ?

በራሴ ጥሩ ነገር እንደምንሰራ አስባለው፡፡ በሁሉም ቦታዎች ላይ ያሉት ተጫዋቾች ጥሩ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ጥሩ አሰልጣኝ አለን፡፡ የልጆቹም አንድነት በጨዋታው ጥሩ ነገር እንድናይ ያስችለናል ብዬ አስባለው፡፡ በመጀመሪው ጨዋታ በነሱ ሜዳ የማይገባ ነጥብ ጥለን አሁን ላይ ላለው ሁኔታ ትንሽ የሚያስቆጭ ነገር አስተምሮናል፡፡ አንዳንዴ እግርኳስ ላይ እንዲህ ያጋጥማል፡፡ ነገሮችን እንደዚህ ይሆናሉ ብለን አለማሰባችን መጀመሪያ ላይ ነጥብ እንድንጥል ያደረገን ምክንያት ነው፡፡ ግን በመልሱ ጨዋታ የተለየ ነገር ይኖራል ብዬ አስባለው፡፡”

ወደክለብ ህይወት ልውሰድህ፡፡ በፔትሮጀት ያለህን ቆይታ ለሁለት ዓመታት አራዝመሃል. . .

“ለረጅም ግዜያት ክለቡ እያነጋገረኝ ነበር፡፡ እኔ ግን ክለብ መቀየር ስለፈለግኩ ትንሽ ነገሮችን አዘግይቼ ነበር፡፡ ያው አንድ ዓመት ውል እያለኝ ነው ሁለት ዓመት የጨመርኩት፡፡ ዕድሎች እና አማራጮች ብዙ ቢኖሩክ አማራጮቹን ትጠቀማለህ፡፡ እነደዚህ ዓይነት ዕድል ሲመጣልህ ይህንን ዕድል መሸሽ የለብህም ይህንን ዕድል መጠቀም አለብህ፡፡ የዝውውሩ አቀያየር ነው እንጂ አሁንም ፈረምክ ውልህ አልቆ ፈረምክ ለውጡ አንድ ነው፡፡ ውሉ ቢታደስም ሌሎች የተሻሉ አማራጮች ሲመጡ ከክለቡ ጋር ተደራድሬ የምሄድበት ምክንያቶች አሉ፡፡ ይህንን እንደአማራጭ ይዤ ነው ውል ያራዘምኩት፡፡ በአንድ ዓመት ውስጥ ጥሩ ነገር ካሳየው እኔን የሚፈልገኝ ክለብ ከፔትሮጀት ጋር ተደራድሮ የምሄድበት መንገድ ይኖራል፡፡ ውል በማራዘሜ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡”

ግብፅን ጨምሮ በተጫወትክባቸው የአፍሪካ ሃገራት ሊጎች ላይ ጥሩ ጊዜያት አሳልፈሃል፡፡ ምን ይሆን ሚስጥሩ?
“እግርኳስ ተጫዋች ስትሆን በውስጥህ ጥንካሬ ሊኖርህ ይገባል፡፡ ትግስተኛ መሆን አለብህ፡፡ ብዙ ችግሮች ያጋጥሙሃል፡፡ ችግሮችን መቋቋም አለብህ፡፡ የሚያጋጥሙ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ዛሬ ገብቼ ጥሩ ነገር ላልሰራ እችላለው ፤ ነገ ደግሞ ጥሩ ነገር ልሰራ እችላለው፡፡ ይህ በአዕምሮዬ ካለ ምንም የሚያቅተኝ ነገር የለም፡፡ ባጋጣሚ ከጊዮርጊስ እንደወጣሁ ሊቢያ ነው የሄድኩት፡፡ ሊቢያ ጥሩ ግዜ አሳልፌ ነበር ነገርግን የብሄራዊ ቡድን ጨዋታዎች ሲበዙ እኔም ትኩረቴን ለብሄራዊ ቡደን ነበር የምሰጠው፡፡ ከክለቤ (አል ኢትሃድ ትሪፖሊ) ጋር የነበረው ግንኙነት እየቀዘቀዘ ነበር፡፡ ከክለቤ ጋር ጥሩ አልነበርኩም፡፡ አሰልጣኙም ክብር የለውም ብሎ ነው ያልተስማማነው፡፡ ወደ ሱዳን ሳመራ ግን ነገሮች ቀለውኝ ነበር፡፡ አስታውሳለው በአንድ ጨዋታ አምስት ግብ እንዳስቆጠርኩ፡፡ በሜሪክ በፊት የነበረው አሰልጣኝ (ሚካኤል ክሩገር) ክለቡን ሲለቅ እና አዲስ አሰልጣኝ ሲመጣ ብዙ ችግሮችን አየሁ፡፡ ልምምድ ላይ አልቀልድም እሰራለው፡፡ መለወጥ እና ጥሩ ደረጃ መድረስን እፈልጋለው፡፡ በድንገት ዕድል ሳገኝ የግብፁ ዝውውር ተሳካ፡፡ ኳስ ተጫዋች ስትሆን እድልም ያስፈልገሃል፡፡ እድልም ሲመጣ በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ በግብፅ ሁለት ዓመት በጥሩ ሁኔታ አሳልፌያለው፡፡ በመጀመሪያው አመት ጥሩ ተንቀሳቅሻለው፡፡ በመጀመሪያው ዓመት መጨረሻ አከባቢ በተወሰነ የድርድር ችግር ነው እንጂ ወደ ስፖርቲን ሊዝበን የምሄድበት አማራጮች ነበሩ፡፡ ይህ ነገር በመፈጠሩ አዝኛለው፡፡ ዕድሉም በመምጣቱ በጣም ደስተኛ ነበርኩ ለምን እንደዚህ አይነት እድል አገኛው ብዬ አላስብም፡፡ በሁለተኛ ዓመት ቆይታዬ ገባ ወጣ ያለ ነገር ነበር፡፡ አሰልጣኞች ሲቀያየሩ የራሳቸውን አጨዋወት ይዘው ስለሚመጡ ትንሽ ያስቸግራል፡፡ አሰልጣኙ በእኔ ላይ ዕምነቱን ሲጥል ወደ መጨረሻው ጨዋታ አከባቢ ግቦች ማስቆጠር ጀመርኩ፡፡ እኔ ከአሰልጣኙ ጋር መቀጠል አልፈለግም ነበር፡፡ ይህንን ከዚህ ቀደም በሰጠኀችሁ ኢንተርቪው ነግሪያችሁ ነበር፡፡ ያው የአሰልጣኙ ዕምነት ሲመጣ ነው ለመቀጠል የወሰንኩት፡፡”

አዲሱ የውድድር ዘመን በመስከረም ወር መጀመሪያ ይጀመራል፡፡ ሽመልስ በግሉ እና ከክለቡ ጋር ምን አቅዷል?

“አሁን ላይ ብዙ ጫና እንደሚበዛብኝ አውቃለሁ፡፡ ውሌን ሳራዝም ለመጀመሪያ ግዜ እኔ ነኝ ክለቡ ከተመሰረተ ከፍተኛ ክፍያ የተከፈለኝ፡፡ እነሱ ስለዚህ ክፍያ እንደሚያስቡ አውቃለው፡፡ እኔንም አስቀድሜ አንዳስብ ነው ያደረገኝ፡፡ ለክለቤ የሆነ ነገር አደርጋለው ብዬ አስባለው፡፡ ለምን እኔ ላይ ጫና እንዳለ አውቃለው፡፡ አዳዲስ ተጫዋቾች በየዓመቱ ይመጣሉ፡፡ ከሲኒየሮቹ ጋር ትግባባለህ ፤ ከአዳዲሶቹ ጋር ለመግባባት ደግሞ ትንሽ ግዜን ይጠይቃል፡፡ ከአዳዲሶቹ ጋር ለተወሰነ ግዜ አብሬ ዝግጅት አድርጊያለው፡፡ ሁሉንም ሊጉ ሲጀመር የምናውቀው ይሆናል፡፡ የግብፆች አጨዋወት ስርዓት ትንሽ ይከብዳል፡፡ በታክቲክ የታጠረ ነው ጉልበትም ይበዛዋል፡፡ ከአምላክ ጋር ጥሩ ነገር አደርጋለው ብዬ አስባለው፡፡”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *