“በእግርኳስ ዝቅተኛ ግምትን ማግኘት የተሻለ ነው” የሲሸልስ አሰልጣኝ ራልፍ ጅያን ሉዊ

የሲሸልስ ብሄራዊ ቡድን 19 ተጫዋቾችን እና ሶስት የአሰልጣኝ አባላትን ብቻ በመያዝ ሃሙስ አመሻሽ አዲስ አበባ የገባ ሲሆን ዛሬ ወደ ሃዋሳ በማቅናት 11፡00 ሰዓት ላይ የመጀመሪያ ልምምዱን አድርጓል፡፡ ሲሸልስ በአራት ነጥብ በሶስተኛ ደረጃ ላይ ስትገኝ ከዋሊያዎቹ ጋር ቪክቶሪያ ላይ 1-1 መለያየት ችላለች፡፡

ለአጭር ግዜ ብሄራዊ ቡድኑን ያዘጋጁት አሰልጣኝ ራልፍ ጅያን ሉዊ ስለቡሄራዊ ቡድኑ ዝግጅት እና ስለኢትዮጵያው ጨዋታ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርገዋል፡፡

ዝግጅታቹ ምን ይመስል ነበር?

ዝግጅታችን ረጅም አልነበረም፡፡ ከዕሁድ ጀምሮ ነው ጥሩ ዝግጅት የነበረን፡፡ ባሳለፍነው ቅዳሜ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ስለነበሩ ተጫዋቾችን የሰበሰብነው ዕሁድ ነበር፡፡ ሁለት የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን ሰኞ እና ማክሰኞ መጫወት ችለናል፡፡ ሃሙስ ነው ወደ ኢትዮጵያ የመጣነው፡፡ ዛሬም ልምምድ አድርገናል፡፡ ጥሩ ጨዋታ እና ጥሩ እንቅስቃሴ እንደምናሳይ ተስፋ አለኝ፡

የሲሸልስ ሊግ ተጀምሯል እና ከሊጉ አዳዲስ ተጫዋቾችን ለመምረጥ ችላችኋል?

አዎ ሶስት አዳዲስ ተጫዋቾችን በቡድኑ አካተናል፡፡ አንድ ጀርመን የሚጫወት ተጫዋችንም በስብስባችን አካተናል፡፡ በአካል ብቃት ሁሉም ተጫዋቾቻችን ብቁ እንደሚሆኑ እንተማመናለን ምክንያቱም የሊግ ጨዋታዎች እየተደረገ ስለሆነ፡፡ ይህ የአካል ብቃት ደረጃችን ለቅዳሜው ጨዋታ እንደሚያግዘን ተስፋ አለኝ፡፡

ወደ ኢትዮጵያ ስትመጣ ይህ የመጀመሪያ አይደለም፡፡ ሴንት ሚሸልን ይዘህ በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ቅዱስ ጊዮርጊስን ገጥመሃል እና ስለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ምን አስተያየት አለህ?

ኢትዮጵያ እንደማውቀው አጫጭር ኳስን መሰረት ያደረገ ጨዋታን ትከተላለች፡፡ ፈጣን ተጫዋቾች ያሉት ቡድን ነው፡፡ በእርግጠኛነት የኳስ ቁጥጥር የበላይነት እና ታክቲካል የሆነ ጥሩ ጨዋታን እንደምንመለከት ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ቢሆንም በእራሳችን ታክቲክ ደጋፊውን ሊያዝናና የሚችል ነገር ለማሳየት እንጥራለን፡

ብዙዎች የመሸነፍ ቅድመ ግምቱን ለሲሸልስ ሰጥተዋል፡፡ ሲሸልስ ለኢትዮጵያ ቀላል ተጋጣሚ ትሆናለች?

በእግርኳስ ዝቅተኛ ግምትን ማግኘት የተሻለ ነው፡፡ ምንም ነገር አንፈልግም ስለዚህም ጫና ውስጥ አይደለንም፡፡ ስለዚህም ለራሳችን ጥሩ ነገር ለማሳየት ነው የመጣነው፡፡ ውጤቱ እኛ የምንፈልገው ሆነም አልሆነም እራሳችንን እንድናሻሻል ይረዳናል፡፡

ካርል ሃል በቡድኑ ተካቷል?

ካርል በእንግሊዝ የሙከራ ግዜን እያሳለፈ ስለሆነ ወደ ብሄራዊ ቡድን አልመጣም፡፡ ይህ ለቡድኑ ጥሩ አይደለም፡፡ ከሁለት ሳምንት በኃላ ይመለሳል ለአሁን ግን ወደ ብሄራዊ ቡደን መምጣት አልቻለም፡፡”

እንዳየነው ከሆነ ብሩኖ ሳኢንዲኒ ረዳት አሰልጣኝ ነው፡፡ የሁለተቹ የስራ ግንኙነት ምን ይመስላል?

ብሩኖ ማዳጋስካራዊ ነው፡፡ በተጫዋችነት አብረን ተጫውተናል፡፡ አብረን የአሰልጣኝነት ኮርሶች ወስደናል፡፡ ሲሸልስ ከኢትዮጵያ 1-1 ስትለያይ ብሩኖ የቡድኑ አሰልጣኝ ነበር፡፡ እኔ ለብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ባመለክትም ስራውን ገና አላገኘሁም ነበር ስለዚህ ብሩኖ በስራው ላይ ነበር፡፡ የሱ በእግርኳስ ላይ ያለው ዕውቀት ለቅዳሜው ጨዋታ የሚጠቅመን ይሆናል፡፡

19 ተጫዋቾችን እና 3 የአሰልጣኝ አባላት ብቻን ነው ይዛችሁ የመጣችሁት. . .

የህክምና ባለሙያዎቹ የስራ ፍቃድ አልተሰጣቸውም፡፡ ነገሮችን ለመለወጥ የነበረን ግዜ አጭር ነበር፡፡ ነገርግን ከረዳቶቼ መካከል አንዱ ስለህክምና ሙያ ዕውቀት አለው፡፡ ስለዚህም ህክምናውንም ጨምሮ ደርቦ እየሰራ የሚያግዘን ይሆናል፡፡

እነዚህ ሁሉ ችግሮች ማለፍ ለሲሸልስ ብሄራዊ ቡድን ለነገው ጨዋታ መነሳሳት ይሆናሉ?

አዎ ይሆናሉ፡፡ ለጨዋታው በጥሩ መነቃቃት ላይ እንገኛለን፡፡ ለእራሳችን ጥሩ ነገር እንደምናሳይ ተስፋ አደርጋለው፡፡

Leave a Reply