በ2005 የውድድር አመት መጠናቀቅ ባለመቻሉ ወደ 2006 የተሸጋገረውን የኢትዮጵያ ዋንጫ ያሸነፈው መከላከያ በኮንፌድሬሽን ዋንጫ የመጀመርያ ጨዋታ ከሜዳው ውጪ የኬንያውን ውጤታማ ክለብ ሊዮፓርድስን ይገጥማል፡፡ በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ 3ና ደረጃ ላይ የተቀመጠው ‹‹ጦሩ›› ዘንድሮ መልካም አቋም ላይ የሚገኝ ሲሆን ጨዋታውን በኬንያ ጨርሰው ለመምጣት እንደተዘጋጁ አሰልጣኝ ገብረመድን ኃይሌ እና አማካዩ አብርሃም ይስሃቅ ተናግረዋል፡፡
በመከላከያ በኩል የአጥቂው ማናዬ ፋንቱ እና የመስመር ተከላካዩ ሽመልስ ተገኝ በጉዳት ምክንያት የመሰለፋቸው ጉዳይ አጠራጣሪ ሲሆን ሌላው የመስመር ተከላካይ ሲሳይ ደምሴ በቅጣት የእሁዱ ጨዋታ ያመልጠዋል፡፡ በአጥቂ መስመሩ ጉልህ ችግር እንዳለባቸው የተናገሩት አሰልጣኝ ገብረመድን አዲሱ ፈራሚያቸው ሙሉአለም ጥላሁን ክፍተቱን እንደሚደፍን ተስፋ አድርገዋል፡፡
መከላከያ ዛሬ ረፋዱ ላይ ወደ ናይሮቢ የተጓዘ ሲሆን እሁድ በ10 ሰአት የ13 ጊዜ የኬንያ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮኑ ሊዮፓርድስን ይገጥማል፡፡
ጠቃሚ ነጥቦች
መከላከያ በኮንፌድሬሽን ዋንጫው ሲሳተፍ የዘንድሮው ከ7 አመታት በኃላ ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡ በ1999 በአስራት ኃይሌ እየተመራ 1ኛው ዙር ደርሶ በሩዋንዳው አትራኮ ተሸንፎ ከውድድር መውጣቱ ይታወሳል፡፡
ሊዮፓርድስ ለኢትዮጵያ ክለቦች አዲስ አይደለም፡፡ በ2002 አም. በኮንፌዴሬሽን ካፑ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ባደረገው ጨዋታ በድምር ውጤት 4-3 ተሸንፎ ከውድድር መውጣቱ አይዘነጋም፡፡
{jcomments on}