ለቀጣይ አሰልጣኝነት 4 አሰልጣኞች ፍላጎት አሳይተዋል

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ረቡእ እለት አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻውን አባሮ በ8 ቀናት ውስጥ ቀጣዩን ‹‹ የሚፋጅ ወንበር ›› የሚረከብ አሰልጣኝ እንደሚለይ ማሳወቁን ተከትሎ ሁለት የሃገር ውስጥ እና ሁለት የባህር ማዶ አሰልጣኞች ለቦታው ፍላጎታቸውን አሳይተዋል፡፡

ከአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በፊት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን ለ4 ወራት በጊዜያዊነት ያሰለጠኑት ቤልጅየማዊው ቶም ሴይንትፌይት ዋልያዎቹን መረከብ እንደሚፈልጉ ለሱፐር ስፖርት ተናግረዋል፡፡ ‹‹ ኢትዮጵያ ምርጥ ቡድን አላት፡፡ በዚህ ቡድን ኢትዮጵያን ወደላቀ ምእራፍ እንደማሸጋግራት አምናለሁ፡፡›› ያሉት ቤልጅየማዊው ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በርካታ የአፍሪካ ብሄራዊ ቡድኖችን በማሰልጠናቸው ለአፍሪካ የእግርኳስ ባህል ቅርብ ናቸው፡፡ የ40 አመቱ አሰልጣኝ በኦክቶበር መጨረሻ ከፌዴሬሽኑ ጋር በፈጠሩት አለመግባባት ከዋልያዎቹ ጋር መለያየታቸው ይታወሳል፡፡

የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ስሬድዮዚች ሚሉቲን ‹‹ሚቾ››ም ዋልያዎቹን የመረከብ ፍለጎት እንዳሳዩ እየተነገረ ነው፡፡ ሰርቢያዊው አሰልጣኝ በቅዱስ ጊዮርጊስ 5 የውድድር ዘመናት ቆይታቸው በሁሉም አመታት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ያነሱ ሲሆን ክለቡን ለሴካፋ ክለቦች ሻምፒዮና ፍፃሜም አድርሰውታል፡፡ ከኢትዮጵያዊቷ ባለቤታቸው 3 ልጆች ያፈሩት ሚቾ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ትክክለኛው ሰው ቢመስሉም ከኡጋንዳ ብሄራዊ ቡድን ጋር ያላቸው ኮንትራት እክል ሊፈጥር ይችላል፡፡

ዘንድሮ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መልካም ጊዜ እያሳለፉ የሚገኙት አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነ ማርያምም ፍላጎት ካሳዩት ውስጥ ተካተዋል፡፡ በትራንስ ኢትዮጵያ ፤ ሐረር ቢራ ፤ ኢትዮጵያ ቡና እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የማሰልጠን የ10 አመታት ልምድ ያላቸው አሰልጣኝ ፀጋዬ ዋልያዎቹን ሊረከቡ እንደሚችሉ በብዙዎች ዘንድ ግምት እየተሰጣቸው ነው፡፡ በሐረር ቢራ የሚያውቋቸው የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ችሎታቸውን ጠንቅቀው ቢያውቁም የአሰልጣኙ በትልቅ ደረጃ የማሰልጠን ልምድ አለመኖር ከፍተኛ ጫና ላለበት ስራ ለመመረጥ እክል ይፈጥርባቸዋል፡፡

የአልአህሊ ሼንዲው ምክትል አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ሌላው ዋልያዎቹን ሊረከቡ የሚችሉ አሰልጣኝ ናቸው፡፡ በ2003 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ያነሱት አሰልጣኝ በሱዳኑ ክለብ 2ኛ የውድድር ዘመናቸውን የጀመሩ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጥሪ ከደረሳቸው አዎንታዊ ምላሻቸውን ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ውበቱ በአዳማ ከነማ እና ኢትዮጵያ ቡና ስኬታማ አመታትን ሲያሳልፉ በንግድ ባንክ አስቸጋሪ የውድድር ዘመን አሳልፈዋል፡፡

የእግርኳስ ፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ከዋናው ብሄራዊ ቡድን በተጨማሪ ከ20 እና ከ17 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኞች እንደሚሾሙ አስታውቀዋል፡፡