ከነሃሴ 4-29 ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች በሆኑ በ57 ቡድኖች መካከል የተደረገው ዓመታዊው የክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ውድድር ዛሬ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡ በፍፃሜው ጨዋታ አፍሮ ፅዮን ጫካ ሜዳን በመለያ ምት 6-5 በማሸነፍ የዋንጫ አሸናፊ ሆኗል፡፡ ለደረጃ በተደረገው ጨዋታ ደግሞ መንግስቱ እና ልጆቹ በመለያ ምት አሰላ (የነገ ፍሬዎች) 5-4 ማሸነፍ ችለዋል፡፡
መንግስቱ እና ልጆቹ ከአሰላ (የነገ ፍሬዎች) ለደረጃ ባደረጉት ጨዋታ መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ግዜ 1-1 ተለያይተው አሸናፊውን ለመለየት በተደረገው የመለያ ምት መንግስቱ እና ልጆቹ አሰላን 5-4 በማሸነፍ የሶስተኛ ደረጀን ማግኘቱን አረጋግጧል፡፡
በፍፃሜው የተገናኙት አፍሮ ፅዮን እና ጫካ ሜዳ ነበሩ፡፡ ልክ እንደ ደረጃ ጨዋታ ሁሉ የፍፃሜው ጨዋታ በመደበኛው ክፍለግዜ ሁለቱም ቡድኖች ጨዋታዎችን 1 አቻ በሆነ ውጤት የጨረሱ ሲሆን አፍሮ ፅዮን በመለያ ምት 6-5 በማሸነፍ የውድድሩ ሻምፒዮን ሆኗል፡፡
በውድድሩ መዝጊያ ላይ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር የቦርድ አባል አቶ ዳዊት ውብሸት እና የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን በቀለ ተገኝተዋል፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ይህንን ውድድር በአቶ ይድነቃቸው ተሰማ ስም በመሰየም ለ11 ግዜ ያካሄደ ሲሆን ውድድሩ በርካታ ታዳጊዎች እይታ እንዲያገኙ ማድረግ ችሏል፡፡
አቶ ይድነቃቸው በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ እግርኳስ ላይ ጉልህ አሻራ ያሳረፉ ታላቅ የእግርኳስ ሰው የነበሩ ሲሆን ከካሜሮናዊው ኢሳ ሃያቱ በፊት የካፍ ፕሬዝደንት እንደነበሩ ይታወቃል፡፡
የውድድሩ ተሸላሚዎች
ኮከብ ግብ አስቆጣሪ – ፉአድ አብደላ (አፍሮ ፅዮን በ6 ጎል )
ኮከብ ተጫዋች – ዮሴፍ ተሾመ (መንግስቱ እና ልጆቹ)
ኮከብ አሰልጣኝ – ቶማስ (አፍሮ ፅዮን)
ልዩ ተሸላሚ
የውድድሩ አዘጋጅ አካል ለዓመታት በጫካ ሜዳ ታዳጊዎችን በማፍራት ትልቅ አስተዋፅኦ ትጓደል ምኑየለትን ልዩ ተሸላሚ አድርጎ ሸልሟል፡፡