ጋቦን ለምታስተናግደው የ2017 ቶታል አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የተደረጉ የመጨረሻ የምድብ ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ በተለያዩ የአፍሪካ ከተሞች ተደርገዋል፡፡ ዩጋንዳ ከ39 ዓመት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ስተመለስ ቶጎ ጅቡቲን 5-0 በማሸነፍ ከምድብ አንድ በጥሩ ሁለተኝነት አልፋለች፡፡ በጥሩ ሁለተኝነት የማለፍ ጠባብ ዕድል የነበራት ኢትዮጵያ በየሁለት ዓመቱ ለሚደረገው ወደ አህጉሪቱ ታላቅ ውድድር ማለፍ ሳትችል ቀርታለች፡፡
ዩጋንዳ ኮሞሮስን በፋሩክ ሚያ ግብ 1-0 በማሸነፍ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፏዋን አረጋግጣለች፡፡በኖምቦሎ በተደረገው ጨዋታ ዩጋንዳ ከ1978 በኃላ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ ችላለች፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊሱ ተከላካይ አይዛክ ኢሴንዴ በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ የነበረ ሲሆን በሰርቢያዊው አሰልጣኝ ሰርዮቪች ሚቾ ሚሉቲን የሚመራው ብሄራዊ ቡድን በስኬት ጎዳና ላይ መሄዱን ቀጥሏል፡፡ ዩጋንዳ የሴካፋ ሲኒየር ቻሌንጅ ካፕ ሻምዮን ስትሆን ከምስራቅ አፍሪካ በአለም ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ ድልድል ውስጥ መግባት የቻለች ብቸኛው ሃገር ናት፡፡ ዋጋዱጉ ላይ በተደረገው የምድቡ ሌላ ጨዋታ ቡርኪና ፋሶ ቦትስዋናን 2-1 አሸንፋ ምድቡን በበላይነት መጨረስ ችላለች፡፡ በጨዋታው ላይ ከቦትስዋና 2 እንዲሁም ከቡርኪናፋሶ 1 ተጫዋች በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥተዋል፡፡ ዩጋንዳ ለመጨረሻ ግዜ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ያለችው በማጣሪያው ኢትዮጵያን 2-1 በማሸነፍ ነበር፡፡
ጅቡቲን 5-0 የረመረመችው ቶጎ ኢትዮጵያን እ ቤኒን በግብ ክፍያ በመብለጥ ነው መለፍ የቻለችው፡፡ ከቤልጄሚያዊው ቶም ሴንቲፌት ከቶጎ መልቀቅ በኃላ ብሄራዊ ቡድኑ የተረከቡት አሰልጣኝ ክላውድ ለርዋ ቶጎን ለአፍሪካ ዋንጫው አብቅተዋል፡፡ በምድቡ ሌላ ጨዋታ የካርቴጅ ንስሮቹ ቱኒዚያዎች ላይቤሪን 4-1 በማሸነፍ የምድብ አንድ የበላይ በመሆን የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎዋን አረጋግጣለች፡፡
የኬሌቼ ኢያናቾ ድንቅ ግብ ናይጄሪያን በታንዛኒ ላይ አሸናፊ አድርጓታል፡፡ ከምድቡ ግብፅ አስቀድማ በማለፏ ውጤቱ ጠቃሚ አልነበረም፡፡ በኢትዮጵያ ምድብ የምትገኘው አልጄሪያ ሌሶቶን 6-0 አሸንፋለች፡፡ ሂላል ኤል አረብ ሱዳኒ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር በሰባት ግቦች የምድብ ማጣሪያው ኮከብ ግብ አግቢ መሆን ችሏል፡፡ በስደስት ተከታታይ የኢንተርናሽናል ጨዋታዎች ስምንት ግቦች ያስቆጠረው የዋሊያዎቹ አጥቂ ጌታነህ ከበደ ስድስት ግቦችን በማጣሪያው ማስቆጠር ችሏል፡፡
ኬፕ ቬርድ በሊቢያ 1-0 በመሸነፏ በጥሩ ሁለተኝነት የማለፍ ተስፋዋን አበላሽታለች፡፡ ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ በመራው ጨዋታ የሊቢያ ማሸነፊያ ግብ ፉአድ አል ቲሪኪ በ90ኛው ግብ ከመረብ አዋህዷል፡፡
የመጨረሻ ማጣሪያ ጨዋታ ውጤቶች ይህንን ይመስላሉ
አልጄሪያ 6-0 ሌሶቶ
ኢትዮጵያ 2-1 ሲሸልስ
ሞሮኮ 2-0 ሳኦቶሜ እና ፕሪንስፔ
ቱኒዚያ 4-1 ላይቤሪያ
ቶጎ 5-0 ጅቡቲ
ማሊ 5-2 ቤኒን
ጊኒ 1-0 ዚምባቡዌ
ዲ.ሪ. ኮንጎ 4-1 ማዕከላዊ የአፍሪካ ሪፐብሊክ
ኤኳቶሪል ጊኒ 4-0 ደቡብ ሱዳን
ኮንጎ ብራዛቪል 1-0 ጊኒ ቢሳው
ዛምቢያ 1-1 ኬንያ
ቡርኪናፋሶ 2-1 ቦትስዋና
ዩጋንዳ 1-0 ኮሞሮስ
ማላዊ 1-0 ስዋዚላንድ
ኮትዲቯር 1-0 ሴራሊዮን
ሴኔጋል 2-0 ናሚቢያ
ሞዛምቢክ 1-0 ሞሪሽየስ
ኬፕቬርድ 0-1 ሊቢያ
ናይጄሪያ 1-0 ታንዛኒያ
አንጎላ 1-1 ማዳጋስካር
ካሜሮን 2-0 ጋምቢያ
ደቡብ አፍሪካ 1-1 ሞሪታንያ
ሱዳን 1-2 ጋቦን
ያለፉ ሃገራት
ጋቦን (አዘጋጅ)፣ አልጄሪያ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ካሜሮን፣ ኮትዲቯር፣ ዲ.ሪ. ኮንጎ፣ ግብፅ፣ ጋና፣ ጊኒ ቢሳው፣ ማሊ፣ ሞሮኮ፣ ሴኔጋል፣ ቱኒዚያ፣ ዚምባቡዌ፣ ዩጋንዳ እና ቶጎ (ሁለቱም በጥሩ ሁለተኝነት)