በዩጋንዳ አስተናጋጅነት ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደው የሴቶች የሴካፋ ውድድር ከመስከረም1 እስከ መስከረም 14 ይደረጋል።
ከሚሳተፉት ሰባት ቡድኖች መካከል በምድብ ሁለት የሚገኘው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን በድሬዳዋ ከተማ ከነሀሴ 13 ጀምሮ በትሪያንግል ሆቴል ከትሞ ዝግጅቱን ሲያከናውን ቆይቶ ከትላንት በስትያ አዲስ አበባ የገባ ሲሆን ትላንት በአበበ ቢቂላ ስታድየም ሊያደርጉት የነበረውን ልምምድ በዝናብ ምክንያት ሳይሰሩ ቀርተዋል።
ብሄራዊ ቡድኑ በዛሬው እለት ከቀኑ ሰባት ሰዓት ጀምሮ ለ45 ደቂቃዎች 24 ተጨዋቾችን በመያዝ በአበበ ቢቂላ ስታድየም ልምምዱን አድርጓል። በዛሬው መርሃ ግብር አሰልጣኝ መሰረት ማኒ ቡድኑን ለሁለት በመክፈል የሟሟሟቂያ ጨዋታ ያደረጉ ሲሆን ሁሉም የቡድኑ አባላት ጥሩ ጤነኝነት ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።
ቡድኑ አርብ ወደ ኡጋንዳ እንደሚጓዝ ተነግሯቸው ወደ አዲስ አበባ ቀደም ብለው የመጡ ቢሆንም ጉዞው ወደ ቅዳሜ መዘዋወሩ ከሙቀት ሀገር ወደ ቀዝቃዛ አካባቢ መጥተው መቆየታቸው አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚፈጥርባቸው ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል።
ቡድኑ በመጪው ቅዳሜ 20 ተጨዋቾችን እና ተያያዥ የቡድኑ ልኡካንን ጨምሮ በአጠቃላይ 26 የልኡካን ቡድኖችን በመያዝ ወደ ስፍራው እንደሚያመራ ለማወቅ ተችሏል።
የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን በምድብ ሁለት ከታንዛኒያ እና ሩዋንዳ ጋር የተደለደለ ሲሆን የመጀመሪያ ጨዋታውን ረቡዕ መስከረም 4 ከሩዋንዳ ጋር በሰሜናዊ ዩጋንዳ በሚገኘው ጂንጃ ከተማ የሚጫወት ይሆናል።
[socialpoll id=”2385802″]
[socialpoll id=”2385807″]