“ለሁሉም ተጋጣሚዎቻችን ክብር አለኝ” መሰረት ማኔ

የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ዩጋንዳ ጂንጃ ላይ ለምታስተናግደው የመጀመሪያው የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ 26 የልኡካን ቡድን በመያዝ ቅዳሜ ወደ ስፍራው  ያቀናል፡፡ ሉሲዎቹ ድሬዳዋ ላይ ዝግጅት እያደረጉ የነበረ ሲሆን 20 ተጫዋቾችን ይዘው ወደ ዩጋንዳ ያቀናሉ፡፡

የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ መሰረት ማኔ ስለዝግጅት እና ስለሴካፋ ዋንጫው ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ስለ ዝግጅት

“ዝግጅት በጣም ጥሩ እና ደስ የሚል ነበር፡፡ ድሬዳዋ ለ15 ቀን ነበርን፡፡ በ15 ቀን ቆይታችን ለቡድኑ አስፈላጊ ነው ያልናቸውን ዝግጅቶች ከአካል ብቃቱም ከታክቲኩም ከቴክኒኩም ሰርተናል፡፡ እንዲሁም ሁለት የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን ከወንድ ቡድኖች ጋር ማድረግ ችለናል፡፡ በሁለቱም ጨዋታ ላይ እያንዳንዱ ተጫዋች የነበረው እንቅስቃሴ በጣም ጥሩ ነበር፡፡”

ስለ ምድባቸው

“እኔ ለሁሉም ቡድን ክብር አለኝ፡፡ እግርኳስ ብዙ ግዜ በተለይም አሁን ያልተጠበቁ ቡድኖች የተለየ ነገር በውድድር ላይ የሚያሳዩበት ግዜ ነው፡፡ ለሁሉም ክብር አለን፡፡ እኛ ግን ሜዳ ገብተን ያለንን ነገር ሁሉ ለመስጠት እና የፈለግነውን ውጤት ለማስመዝገብ ዝግጁ ሁነን ነው ያለነው፡፡”

ስለ ተጋጣሚዎቻችን

“ስለተጋጣሚዎቻችን ያገኘነው መረጃ የለም፡፡ የኬንያ መረጃ አለኝ፡፡ የታንዛያ የተወሰነ መረጃ አለኝ፡፡ ስለሌሎቹ ግን ብዙም መረጃ ማግኘት አልቻልንም፡፡ በቀጣይ ግዜ መረጃዎችን ለማግኘት የተሻለ ጥረት እናደርጋለን፡፡”

የተጫዋች ስብስቡ ወደ 20 ስለመውረዱ

“ያስቸግራል በጣም፡፡ የአመራረጥ ብቻ አይደለም ለልጆቹም ሞራል በጣም ያስቸግራል፡፡ ምንም ችግር የለውም እከሌ እከሌ እከሌ እያልክ ልትወስን ትችላለህ፡፡ እሱ አይደለም የሚከብደው፡፡ ግን ልጆቹ ይህን ያህል ግዜ ቆይተው ከዚህ በኃላ ወደ ውድድር ስፍራ አትሄዱም ስትላቸው ሞራላቸው ላይ የሚፈጠረው እና ከዛ በኃላ ላይ ያለው ነገር ነው ለእኔ የራስ ምታት የሆነብኝ፡፡ ይህ ለእኔ ምቾት አልሰጠኝም ግን ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡ የስብስቡ መጠን ከ23 ወደ 20 ዝቅ ያለበት ምክንያት ሴካፋ ያወጣው ደንብ ላይ ከ20 ተጫዋቾች በላይ እንማይቀበሉ ነው፡፡ እኔ እንደውም እነሱ የ20 ተጫዋቾችን ከሸፈኑ እኛ ደግም የሶስቱን ሸፍነን ለምን ውድድር አንሄድም ብዬ ነበር፡፡ ነገር ግን ሴካፋ ጉዳዩን እንዳልተቀበለ የፌድሬሽኑ ዋና ፀሃፊ ነግረውኛል፡፡ ስለዚህ ይህ ከአቅም በላይ በመሆኑ የልጆቹን ሞራል ጠብቀን ለሚቀጥለውም ይህንን እድል እንደሚያገኙ ታሳቢ አድርገው እንዲመለሱ እና በመልካም እንድንለያይ ጥረት እናደርጋለን፡፡”

በስነልቦና በኩል ስለተሰራው ስራ

“የተሳካ ስራ ተሰርቷል፡፡ ዶክተር ወገኔ እና የህክምና እና የስነልቦና ባለሙያው አስራት (የድሬዳዋ ከተማ የህክምና ባለሙያ ነው) ሁለቱን ጋብዤ በቂ ግዜ ወስደው ለልጆቹ ትምህርት እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡”


[socialpoll id=”2385802″]

[socialpoll id=”2385807″]

Leave a Reply