የ2016 የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ በዩጋንዳዋ ጂንጃ ከተማ በሚገኘው የንጅሩ ቴክኒካል ማዕከል ዛሬ ተጀምሯል፡፡ በመክፈቻው በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ኬንያ አስተናጋጇን ስትረታ ቡሩንዲ ዛንዚባር ላይ የግብ ናዳ አውርዳለች፡፡
በምድብ አንድ የሚገኙት ቡሩንዲ እና ኬንያ ሶስት ነጥብ ይዘው የወጡበት ድል አስመዝግበዋል፡፡ ቡሩንዲ ዛንዚባርን 10-1 በሆነ ሰፊ ውጤት ስትረታ ኬንያ አዘጋጇን ዩጋንዳን 4-0 ረምርማለች፡፡
08:00 ላይ ቡሩንዲ በ10 ተጫዋች አመዛኙን የጨዋታ ክፍለ ግዜ በጨረሰችው ዛንዚባር ላይ የግብ ናዳ አውርዳለች፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ ስድስት እንዲሁም በሁለተኛው አጋማሽ አራት ግብ ያስቆጠሩት ቡሩንዲዎች ምድብ አንድን ከወዲሁ መምራት ጀመረዋል፡፡ የብሩንዲን የድል ግቦች ኡዊሜዛ ድራዚላ (3)፣ አዚዛ ሚሲጊዬማና፣ ኔይላ ኡሚማና፣ ጆይል ቡኩሩ፣ ማጊ ሙሜዚሮ (2) እና ሳኢዲ ሳኪና (2) ከመረብ አዋህደዋል፡፡ ዛንዚባር ከባዶ መሸነፍ ያዳነች ግብ አብደላ አብዱላሂ ሙዋጁማ በፍፁም ቅጣት ምት አስቆጠራለች፡፡ ባለ ሐት-ትሪኳ ጃዚላ በ19ኛው ደቂቃ ያስቆጠረችው የመክፈቻ ግብ የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ የመጀመርያ ግብ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ የዛንዚባሯ ግብ ጠባቂ አሚና መሃመድ ኪታምቢ በቀይ ካርድ በመጀመሪያው አጋማሽ ወጥታለች፡፡
ዛንዚባር ከ30 ዓመት በፊት ያዘጋጀችውን የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ ማሸነፏ የሚታወስ ሲሆን በዘንድሮው ውድድር ግን ያልተቀናጀው ቡድኗ ከምድብ ተሰናባች እንደሚሆን ይገመታል፡፡
10:00 ላይ ከፍተኛ ግምት አግኝቶ የነበረው የአስተናጋጇ ዩጋንዳ እና ለአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ያለፈችው ኬንያ ጨዋታ እንደተጠበቀው ጠንካራ ፉክክር ሳይታይበት በኬንያ 4-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ የኬንያን ግቦች ሜሪ ዋንጂኩ ኪኑቲ፣ ኢስ አኪዳ (2) እና ቪቪያን ኮራዞን በስማቸው አስመዝግበዋል፡፡
ሃራምቤ ስታርሌት በሚል ስም የሚታወቁት ኬንያዎች ከወራት በፊት በወዳጅነት ጨዋታ ዩጋንዳን ናይሮቢ ላይ በተመሳሳይ 4-0 ማሸነፋቸው አይዘነጋም፡፡
ኬንያ ካሜሮን ለምታስተናግደው የ2016 ቶታል የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ያለፈች ብቸኛው የምስራቅ አፍሪካ ቡድን ስትሆን የሴካፋ ሴቶች ዋንጫን የማሸነፍ ቅድመ ግምት ከተሰጣቸው ሃገራት መካከል ትገናለች፡፡
ውድድሩ ነገ ሲቀጥል በኢትዮጵያ ምድብ የሚገኙት ታንዛኒያ እና ሩዋንዳ ይገናኛሉ፡፡ የዚህ ምድብ አራፊ የሆኑት ሉሲዎቹ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ረቡዕ ሩዋንዳን በመግጠም ይጀምራሉ፡፡
ሴካፋ ለተወዳዳሪ ሃገራት እንደማረፊያነት የቀረቡት ክፍሎች በእጅጉ ያስተቸው ሲሆን ኬንያ፣ ኢትዮጵያ እና ሩዋንዳ በማረፉያ ቦታው ላይ ቅሬታቸውን አሰምተዋል ተብሏል፡፡ ኢትዮጵያ ከማረፊያው ወጥታ በሆቴል የተቀመጠች ሲሆን የኬንያ እግርኳስ ማህበርም በተመሳሳይ ብሄራዊ ቡድኑን ከማረፊያ ስፍራው አንስቶ ወደ ሌላ ሆቴል ማዛወሩም ተነግሯል፡፡
ፎቶ – ፉፋ
[socialpoll id=”2385802″]
[socialpoll id=”2385807″]