ሉሲዎቹ የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ ጉዟቸውን በድል ጀመሩ

 ሉሲዎቹ|ዜና| 04-01-2009 


በዩጋንዳ አስተናጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ የመጀመርያውን ጨዋታ ዛሬ ከሩዋንዳ ብሄራዊ ቡድን ጋር ያደረገው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን 3-2 በማሸነፍ ጉዞውን በድል ጀምሯል፡፡

ኢትዮጵያ የሩዋንዳን መረብ ለመድፈር የፈጀባት 3 ደቂቃ ብቻ ነበር፡፡ የፕሪሚየር ሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሎዛ አበራ ከሽታዬ ሲሳይ የተሸገረላትን ኳስ ተጠቅማ ሉሲዎቹን መሪ ማድረግ ችላለች፡፡ ከግቡ መቆጠር በኋላ አመዛኙን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ኢትዮጵያ በርካታ የግብ እድል መፍጠር ብትችልም ግብ ጠባቂዋ ሄሌኔ ግብ ከማድረግ አግዳቸዋለች፡፡ የመጀመርያው አጋማሽ መደበኛ ደቂቃዎች ተጠናቆ 2 ደቂቃዎች ሲጨመሩ ወደ ኢትዮጵያ የግብ ክልል የተላከውን ኳስ ሊያ በአግባቡ ባለመቆጣጠሯ የተገኘውን የማዕዘን ምት ተጠቅማ ሙኪሺማና ዶሪቲ በግንባሯ በመግጨት ሩዋንዳን አቻ አድርጋለች፡፡

picsart_1473866925471

በሁለተኛው አጋማሽ 64ኛው ደቂቃ ሎዛ አበራ በድጋሚ ኢትዮጵያን ቀዳሚ ማድረግ ችላለች፡፡ ለዚህ ግብ መገኘት በድጋሚ አስተዋፅኦ ያደረገችው የፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ ተጫዋች ሽታዬ ሲሳይ ነች፡፡

ከ6 ደቂቃዎች በኋላ ሩዋንዳዎች ያገኙትን ቅጣት ምት አምበሏ ኒግቤራዋ ሲፋ ግሎሪያ በግንባሯ በመግጨት በድጋሚ ሺ-አማቡቪዎቹን አቻ ማድረግ ብትችልም የሩዋንዳዊያን ፈንጠዚያ ከሴኮንዶች መሻገር አልቻለም፡፡ የቀኝ መስመር ተከላካይዋ መስከረም ካንኮ ሩዋንዳዎች የአቻነት ግብ ባስቆጠሩ ቅፅበት ኢትዮጵያን ለድል ያበቃችውን ግብ ከመረብ አሳርፋለች፡፡ ጨዋታውም በኢትዮጵያ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ድሉን ተከትሎ ኢትዮጵያ የመጀመርያ የሴካፋ ጨዋታዎን በድል ከመጀመሯ ባሻገር ወደ ግማሽ ፍጻሜው ማለፏን ስታረጋግጥ ባለፈው ሰኞ በታንዛንያ በተመሳሳይ 3-2 የተረታችው ሩዋንዳ ከምድቧ ተሰናብታለች፡፡

የምድብ ለን የደረጃ ሰንጠረዥ በበላይነት ለማጠናቀቅ ኢትዮጵያ እና ታንዛንያ አርብ የሚያደርጉት ጨዋታ ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ነው፡፡

Leave a Reply