በሴካፋ ሴቶች ዋንጫ ዩጋንዳ ኬንያን ተከትላ ወደ ግማሽ ፍፃሜ አልፋለች

 የሴቶች እግርኳስ | 05-01-2009 

በዩጋንዳ ጂንጃ ከተማ በመደረግ ላይ በሚገኘው የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ ከምድብ አንድ አዘጋጇ ዩጋንዳ ኬንያን ተከትላ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ያለፈች ሁለተኛ ሃገር ሆናለች፡፡ ዩጋንዳ ቡሩንዲን 1-0 ስትረታ ኬንያ አስቀድማ መውደቋን ያረጋገጠችውን ዛንዚባርን 11-0 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፋለች፡፡

የጎል ፌሽታ በነበረበት ጨዋታ ሃራምቤ ስታርሌትስ በሚል ስም የሚታወቁት ኬንያዎች ዛንዚባርን 11-0 መርታት ችለዋል፡፡ በሶሰት ጨዋታዎች ብቻ 30 ግቦችን ያስተናደገው የዛንዚባር ቡድን እስከዕረፍት ድረስ በክርስቲያን ናፉላ ሁለት እና ጃኪ ኦጎል ግቦች 3-0 በኬንያ ተመርቷል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ ኦጎል በፍፁም ቅጣት ምት ለራሷ ሁለተኛውን ለቡድኗ ደግሞ አራተኛውን ግብ ስታስቆጥር ሜርሲ አቼንግ ኦኒያንጎ፣ ቪቪያን ኮራዞን ኦዲአምቦ (ሃት-ትሪክ)፣ ሜሪ ዋንጂኩእና ኢስ አኪዳ (2) ቀሪዎቹን ግቦች አስቆጥሯል፡፡

ኬንያ ምድብ አንድን በ9 ነጥብ ስታጠናቅቅ በሶስቱም ጨዋታ ግብ ያላስተናገደች ብቸኛዋ ሃገር ሆናለች፡፡

picsart_1473971505896

ከምድቡ ኬንያን ተከትሎ አላፊ ቡድኑን ይለያል ተብሎ በተጠበቀው ጨዋታ ዩጋንዳ ብሩንዲን 1-0 አሸንፋለች፡፡ ዩጋንዳዊያን ክረስትድ ክሬንሶቹን ለማበረታታት ወደ ሜዳ የመጡ ሲሆን የፋዚላ ኢክዋፑት ግብ ዩጋንዳን አሸናፊ ለማድረግ በቂ ነበረች፡፡ ሁለቱም ሃገራት ከፍተኛ ፉክክር ያሳዩ ሲሆን አዘጋጇ ሃገር ወደ ግማሽ ፍፃሜው በስድስት ነጥብ ማምራት ችላለች፡፡

ውድድሩ ነገም ሲቀጥል ከምድብ ሁለት ማለፋቸውን ያረጋገረጡት ኢትዮጵያ እና ታንዛኒያ የምድቡን የበላይነት ለመያዝ በንጅሩ ቴክኒካል ማዕከል ይፋለማሉ፡፡ ኢትዮጵያ ኤኳቶሪያል ጊኒ ባስተናገደችው የ2012 የሴቶች አፍሪካ ዋንጫ ላይ ታንዛኒያን በአጠቃላይ ውጤት 3-1 በማሸነፍ ማለፏ የሚታወስነው፡፡

ምድብ ሁለት ከያዛቸው ጠንካራ ብሄራዊ ቡድኖች አንፃር የሞት ምደብ የተባለ ሲሆን ለሴካፋ ሴቶች ዋንጫ አሸናፊነትም ኢትዮጵያ፣ ታንዛኒያ እና ኬንያ ከፍተኛ ግምትን አግኝተዋል፡፡

Leave a Reply