የሴቶች እግርኳስ | 06-01-2009
በዩጋንዳ አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው የሴካፍ የሴቶች ዋንጫ የምድብ ለ የመጨረሻ ጨዋታ ዛሬ ይካሄዳል፡፡
3 ሃገራት ከሚገኙበት ምድብ ለ ኢትዮጵያ እና ታንዛንያ ሩዋንዳን በተመሳሳይ 3-2 ውጤት በመርታት ወደ ግማሽ ፍጻሜው ማለፋቸውን ያረጋገጡ ሲሆን ምድቡን በበላይነት ለማጠናቀቅ ዛሬ 10:00 ላይ በንጂሩ ቴክኒካል ማዕከል ይፋለማሉ፡፡
የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ መሰረት ማኒ ቡድናቸው ታንዛንያን አሸንፎ የምድቡ የበላይ ሆኖ ለማጠናቀቅ መዘጋጀቱን ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡
” እኛ ሁሌም ወደ ሜዳ የምንገባው ለማሸነፍ ነው፡፡ ዛሬም አሸንፈን የምድቡ አንደኛ ሆነን እንጨርሳለን ” ብለዋል፡፡ አክለውም በሩዋንዳው ጨዋታ የታየውን የአጨራረስ ችግር ቀርፈው እንደሚገቡ ተናግረዋል፡፡
” አጨራረስ ላይ የነበረብን ችግር ለመቅረፍ በሚገባ ተነጋግረናል፡፡ በዛሬው ጨዋታ ላይ ተጫዋቾቼ ይህን ችግር አስተካክለው ወደ ሜዳ ይገባሉ፡፡” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
የሉሲዎቹ የቡድን አባላት ለዛሬው የታንዛኒያ ጨዋታ በሙሉ ጤንነት እና ዝግጁነት ላይ ይገኛሉ፡፡