ቻምፒየንስ ሊግ፡ ዛማሌክ እና ዋይዳድ ካዛብላንካ ለፍፃሜ ለማለፍ ይፋለማሉ

 የአፍሪካ እግርኳስ | 06-01-2009 

የ2016 ኦሬንጅ ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የግማሽ ፍፃሜ አንድ ጨዋታ ዛሬ ምሽት አሌክሳንደሪያ ላይ ይደረጋል፡፡ የምድብ አንድ አሸናፊው ዋይዳድ ካዛብላንካ የግብፅ ዋንጫ አሸናፊውን ዛማሌክን በሰሜን አፍሪካ ደርቢ የሚገጥም ይሆናል፡፡ ሁለቱም ክለቦች የየሃገራቸውን ሊጎች በባላንጣዎቻቸው የተነጠቁ ሲሆን የአህጉሪቱን ታላቅ ውድድር የማሸነፍ ፅኑ ፍላጎት አላቸው፡፡

ዛማሌክ የግብፅ ፕሪምየር ሊግን ለከተማ ተቀናቃኙ አል አሃሊ አሳልፎ የሰጠ ሲሆን የካዛብላንካው ክለብ የሞሮኮ ቦቶላ የሊግ ክለብሩን በሞሮኮ መዲናው ክለብ በፉስ ራባት ተቀምቷል፡፡

ዛማሌክ አምስተኛውን የቻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን የሞሮኮውን ራጃ ካዛብላንካን በ2002 አሸንፎ ካነሳ በኃላ ውድድሩን ማሸነፍ ተስኖት ቆይቷል፡፡ ኋይት ናይትስ በሚል ስም የሚታወቀው የካይሮው ሃያል ከ11 ዓመታት በኃላ ለቻምፒየንስ ሊግ ግማሽ ፍፃሜ መድረስ የቻለ ሲሆን ለመጨረሻ ግዜ አራት ውስጥ መግባት የቻሉት በ2005 ነበር፡፡ የአሰልጣኝ ሹም ሽር በማድረግ የሚታወቁት የዛማሌኩ ፕሬዝደንት ሞርታዳ መንሱር ክለባቸው በዚህ የቻምፒየንስ ሊጉ የውድድር ዘመን ብቻ ሶስት አሰልጣኞች ተጠቅሟል፡፡ ክለቡን በግዜያዊነት እያሰለጠኑ የሚገኙት ሞሜን ሱሌማን ሲሆን ክለቡን ለፍፃሜ የማሳለፍ ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው፡፡

የሞሮኮው ሃያል ክለብ ዋይዳድ ካዛብላንካ በዘንድሮው የቻምፒየንስ ሊግ ድንቅ ብቃቱን ያስመሰከረ ሲሆን ሃያሎቹን አል አሃሊን እና ቲፒ ማዜምቤን መፈተን ችሏል፡፡ በዌልሳዊው ጆን ቱሾክ የሚሰለጥነው ክለቡ ምድብ አንድን በአሸናፊነት የጨረሰ ሲሆን በ2011 በቱንዚያው ኤስፔራንስ 1-0 ተሸንፈው ያጡትን የቻምፒየንስ ሊግ ክብር ለማግኘት ወደ ፍፃሜ ማለፍን አላማ አደርገዋል፡፡ በፋብሪስ ኦንዳማ እና ቺሶማ ቺካታራ የሚመራው ጠንካራው የአጥቂ ክፍሉ በስፔን ፕሪሜራሊጋን ከሪያል ማድሪድ ጋር ከ26 ዓመታት በፊት በአሰልጣኝነት ላሸነፉት ቱሾክ ከፍተኛ መነሳሳትን ፈጥሯል፡፡

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ እንዲዳኙ ካፍ የደቡብ አፍሪካ ዳኞች ሾሟል፡፡ የመሃል ዳኛ ዳንኤል ፍሬዘር ቤኔት እና ረዳቶቹ ዛክሄሌ ሲዌላ እና ሞቲቢዲ ኩማሎ ጨዋታው የሚመሩ ይሆናል፡፡

የዛሬ ጨዋታ


5:00 ዛማሌክ (ግብፅ) ከ ዋይዳድ ክለብ አትሌቲክ (ሞሮኮ) (ቦርጅ ኤል አረብ ስታዲየም)

Leave a Reply