የአፍሪካ እግርኳስ | 07-01-2009
የኦሬንጅ ኮንፌድሬሽን ካፕ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ዛሬ በቱንዚያ ሶስ ከተማ በሚደረግ አንድ ጨዋታ ሲጀመር የ2015 ኮንፌድሬሽን ካፕ አሸናፊው ኤቷል ደ ሳህል የ2015 ቻምፒየንስ ሊግ አሸናፊው ቲፒ ማዜምቤን ይስተናግዳል፡፡
ኤቷል እና ቲፒ ማዜምቤ በ2016 መጀመሪያ በካፍ ሱፐር ካፕ ተገናኝተው የዲ.ሪ. ኮንጎው ክለብ ማሸነፍ የቻለ ሲሆን በአመት ውስጥ ለሁለተኛ ግዜ በአህጉሪቱ ሁለተኛ ታላቅ ውድድር የፍፃሜ ግማሽ ተፋላሚ ሆነው ቀርበዋል፡፡
በታዋቂው እና ስኬታማው ቱኒዚያዊ አሰልጣኝ ፋውዚ ቤንዛርቲ የሚሰለጠነው የቱኒዚያው ሻምፒዮን ኤቷል ከጨዋታ ጨዋታ መሻሻልን እያሳየ መጥቷል፡፡ ኤቷል ከምድብ ሁለት ፉስ ራባትን ተከትሎ በሁለተኝነት ያጠናቀቀ ሲሆን የዓምና ክቡሩን ለማስመለስ ቲፒ ማዜምቤን ከውድድር ማስወጣት የግድ ይለዋል፡፡ በፈረንሳዊው ሁበርት ቬሉድ የሚመራው የሉቡምባሺው ክለብ ማዜምቤ የተደበላለቀ የውድድር ዘመን አሳልፏል፡፡ ማዜምቤ ከቻምፒየንስ ሊጉ በዋይዳድ ካዛብላንካ የተሰናበተ ሲሆን ከምድብ አንድ በመሪነት ጨርሷል፡፡ ኤቷል ደ ሳህል ልክ እንደ ማዜምቤ ሁሉ ከቻምፒየንስ ሊጉ በናይጄሪያው ኢኒምባ ኢንተርናሽናል በመለያ ምት ተሸንፎ ወድቋል፡፡ የአምስት ጊዜ የአፍሪካ ሻምፒዮኑ ማዜምቤ በ2013 በቱኒዚያዉ ሴፋክሲየን ተሸንፎ የኮንፌድሬሽን ዋንጫ ማጣቱ የሚታወስ ነው፡፡ ከኤቷል በኩል ቢሩጉዊ እና አህመድ አኪያቺ እንዲሁም ከማዜምቤ በኩል ሬንፎርድ ካላባ እና ጆናታን ቦሊንጊ በጨዋታው ላይ ይጠበቃሉ፡፡
ጨዋታውን የሱዳን ዳኞች እንዲመሩት በካፍ ተመርጠዋል፡፡ የመሃል ዳኛው ኤል ፋዲል መሃመድ ሁሴን እና ረዳቶቹ ዋሊድ አህመድ አሊ እና መሃመድ አብደላ ኢብራሂም ጨዋታውን የሚመሩ ይሆናል፡፡
የዛሬ ጨዋታ
22፡00 – ኤቷል ስፖርቲቭ ደ ሳህል (ቱኒዚያ) ከ ቲፒ ማዜምቤ (ዲ.ሪ. ኮንጎ) (ስታደ ኦሎምፒክ ደ ሶስ)