ሲቲ ካፕ| 07-01-2009
የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌደሬሽን ለ11ኛ ጊዜ የሚካሄደው የአዲስ አበባ ዋንጫ (ሲቲ ካፕ) መስከረም 28 እንደሚጀምር ይፋ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ስምንት ክለቦች የሚካፈሉበት ይህ ውድድር ይፋዊ በሆነ መልኩ የሚሳተፉ ክለቦችን እስካሁን ድረስ ባይሳውቅም ከዚህ በፊት ውድድሩ ላይ ተሳታፊ የነበረው እና የ3 ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ኢትዮጵያ ቡና ተሳታፊ እንደማይሆን ሶከር ኢትዮጵያ ከአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌደሬሽን አረጋግጣለች፡፡
ኢትዮጵያ ቡና በተለያዩ ምክንያቶች በውድድሩ ላይ እንደማይሳተፍ ሀሙስ እለት በይፋዊ የፌስቡክ ገፁ ያስታወቀ ቢሆንም የማይሳተፍበት ምክንያት ሳይገለጽ አልፏል፡፡
ኢትዮጵያ ቡና በገንዘብ እና አሰራር ጉዳዮች ላይ ከፌዴሬሽኑ ጋር ባለው ልዩነት ምክንያት እንደማይካፈል ያስታወቀ ሲሆን በዋነኛነት በአምናው ውድድር ላይ ቡድኑ ሊያገኝ የነበረው የገንዘብ ሽልማት መዘግየቱ ከውድድሩ ውጪ እንዳደረገው ለማወቅ ተችሏል፡፡
በኢትዮጵያ ቡና አለመካፈል ፣ ተክቶ በሚሳተፈው ክለብ ዙርያ ፌዴሬሽኑ በቀጣይ ሳምንት በሚጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ማብራርያ ይሰጣል ተብሏል፡፡
በሌላ የሲቲ ካፕ ዜና ባለፉት ሁለት ውድድሮች የተካፈለው አዳማ ከተማ ውድድሩ ላይ ከሚሳተፉ ተጋባዥ ክለቦች አንዱ መሆኑ ሲረጋገጥ በኢትዮጵያ ቡና ምትክ ውድድሩ ላይ የሚሳተፈውን ክለብ ለመለየት ፌዴሬሽኑ ለተለያዩ ክለቦች ጥያቄ ማቅረበ ታውቋል፡፡ ከነዚህም መካከል ከፍተኛ የደጋፊ ቁጥር ያለው ወላይታ ድቻ የፍቃደኝነት ጥያቄ እንዳቀረበ እና እስካሁን ይፋዊ የሆነ ምላሽ አለማግኘቱን የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌደሬሽን አስታውቋል፡፡