ደቡብ ካስቴል ዋንጫ| 07-01-2009
6 ክለቦችን የሚያሳትፈው የደቡብ ካስቴል ዋንጫ በመጪው መስከረም 24 በሀዋሳ ከተማ እንደሚጀምር የደቡብ ክልል እግርኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡
ቢጂአይ ኢትዮጵያ በካስቴል ቢራ ምርቱ ስፖንሰር ያደረገው ይህ ውድድር እንዲጀመር የታሰበው መስከረም 21 ቢሆንም በሙሉጌታ ምህረት የመሸኛ ጨዋታ ምክንያት በ3 ቀናት እንደተራዘመ ታውቋል፡፡
በፕሪሚየር ሊጉ ደቡብን የሚወክሉት ሀዋሳ ከተማ ፣ ሲዳማ ቡና ፣ አርባምንጭ ከተማ እና ወላይታ ድቻ በውድድሩ ላይ እንደሚካፈሉ የተረጋጠጡ ክለቦች ሲሆኑ የደቡብ እግርኳስ ፌዴሬሽን የቅድመ ውድድር ዘመን ዝግጅታቸውን በሀዋሳ እያካሄዱ ያሉት ኢትዮጵያ ቡና እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በውድድሩ ላይ እንዲሳተፉ ጥያቄ አቅርቧል፡፡ ሁለቱ ክለቦች በቀጣዮቹ ሁለት ቀናት ምላሽ ካልሰጡ ሌላ አማራጭ እንደሚፈልግም ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡
ውድድሩ አምና ሀዋሳ ሴንትራል ዋንጫ በሚል ስያሜ በሴንትራል ሀዋሳ ሆቴል ስፖንሰርነት የተካሄደ ሲሆን ሀዋሳ ከተማ በፍጻሜው ድሬዳዋ ከተማን 3-0 በመርታት ቻምፒዮን መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡