ቻምፒየንስ ሊግ፡ ዜስኮ ዩናይትድ ማሜሎዲ ሰንዳውንስን ረቷል

 የአፍሪካ እግርኳስ | 07-01-2009 

በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ግማሽ ፍፃሜ ንዶላ ላይ ማሜሎዲ ሰንዳውንስን ያስተናገደው ዜስኮ ዩናይትድ 2-1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል፡፡

ዜስኮ ዩናይትድ በሜዳው የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታን በዘንድሮው ውድድር ዓመት ያለመሸነፍ ጉዞን ቢቀጥልም የዚምባቡዌው ኢንተርናሽናል ካማ ቢሊያት ግብ ብራዚሎቹ በሚል ቅፅሎ ስም የሚታወቁት ማሜሎዲ ሰንዳውንሶች ለመልሱ ጨዋታ የተሻለ ዕድል እንዲይዙ አስችሏል፡፡

በመጀመሪያው አጋማሽ ግብ ባልተቆጠረበት የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ጃክሰን ሙዋንዛ አከታትሎ ያስቆጠራቸው ሁለት ግቦች ዜስኮ ዩናይትድ 2-0 እንዲመራ አስችለዋል፡፡ ሙዋንዛ በ55ኛው ደቂቃ ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ በመግጨት ሲያስቆጥር  ከደቂቃ በኃላ ሁለተኛውን ግብ ከርቀት የተመታውን ቅጣት ምት በመንካት ከመረብ አዋህዷል፡፡ በ2016 ድንቅ ብቃቱን ለክለቡ እና ሃገሩ እያሳየ የሚገኘው ቢሊያት የጨዋታው መገባደጃ በተቃረበበት ወቅት ለብራዚሎቹ ወሳኝ ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡ ውጤቱ ከሜዳቸው ውጪ ግብ ላስቆጠሩት ማሜሎዲ ሰንዳውንስ መልካም ሲሆን በመልሱ ጨዋታ ለሁለቱም ክለቦች ወሳኝ ነው፡፡

የግማሽ ፍፃሜ የመልስ ጨዋታዎች በሚቀጥለው ሳምንት ቅዳሜ የሚደረጉ ይሆናል፡፡ አሰልጣኝ ጆን ቱሻክን ያሰናበተው ዋይዳድ ካዛብላንካ ዛማሌክን ሲያስተናግድ ዜስኮ ዩናይትድ ወደ ደቡብ አፍሪካ አቅንቶ ማሜሎዲ ሰንዳውንስን ይገጥማል፡፡ ዋይዳድን 4-0 የረታው ዛማሌክ ለፍጻሜ የማለፍ የተሻለ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

የዛሬ ውጤት

ዜስኮ ዩናይትድ (ዛምቢያ) 2-1 ማሜሎዲ ሰንዳውንስ (ደቡብ አፍሪካ)

(55’ 56’ ጃክሰን ሙዋንዛ  87’ ካማ ቢሊያት)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *