የሴቶች እግርኳስ | 07-01-2009
የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ ወደ ወሳኝ ምዕራፍ ተሸጋግሯል፡፡ ነገ የሚደረጉት ሁለት የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ወደ ፍጻሜ የሚያልፉትን ሃገራትን ይለያሉ፡፡
በእጣ የምድቧን ሁለተኛ ደረጃ ይዛ ያጠናቀቀችው ኢትዮጵያ የውድድሩ አሸናፊነት ቅድሚያ ግምት የተሰጣት ኬንያን ነገ 07:30 ላይ ትገጥማለች፡፡
ኬንያ ካሜሩን በምታስተናግደው የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ተሳታፊ መሆኗን ያረጋገጠች ብቸኛ የምስራቅ አፍሪካ ሀገር ስትሆን ያለፈችውም ኢትዮጵያን ጥላ ያለፈችው አልጄርያን አሸንፋ ነበር፡፡ ኬንያ በሴካፋ ባደረገቻቸው 3 ጨዋታዎች 19 ግቦችን ተጋጣሚዋ ላይ ስታስቆጥር ምንም ግብ ሳታስተናግድ በአስፈሪ ወቅታዊ አቋም ላይ ትገኛለች፡፡
በምድብ ለ ሩዋንዳን 3-2 አሸንፋ ከታንዛኒያ አቻ የተለያችው ኢትዮጵያ ከኬንያ በመቀጠል ለዋንጫው ከፍተኛ ግምት ያገኘች ሃገር እንደመሆኗ የነገው ጨዋታ ከፍጻሜ በፊት የሚደረግ ሌላ የፍጻሜ ጨዋታ እንደማለት ነው፡፡ የኢትየጵያ አሰልጣኝ መሰረት ማኒም ጨዋታው ጠንካራ እንደሚሆን ግምታቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡ ” ጨዋታው ጠንካራ ፉክክር እና ጥሩ ጨዋታ የሚታይበት ይሆናል ” ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ እና ኬንያ ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት በ2012 አዲስ አበባ ላይ በወዳጅነት ጨዋታ ሲሆን ሉሲዎቹ 5-0 ማሸነፍ ችለው ነበር፡፡ በሴካፋው ውድድር አድናቆት የተቸራት ሽታዬ ሲሳይ በወቅቱ 3 ግቦች አስቆጥራ ሐት-ትሪክ መስራቷ የሚታወስ ሲሆን ኬንያ በ20 አመታት ውስጥ የደረሰባት ከፍተኛው ሽንፈት ሆኖ ተመዝግቦ ነበር፡፡
አሰልጣኝ መሰረት ቡድናቸው አሁንም ኬንያን ለማሸነፍ እንደተዘጋጁ ተናግረዋል፡፡ ” ያለንን አቅም ሁሉ ተጠቅመን ውጤታማ ለመሆን በሚገባ ተዘጋጅተናል፡፡ ጥሩ ነገር ይኖራል ብዬ አስባለው”
የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች
07:30 ኬንያ ከ ኢትዮጵያ
09:30 ዩጋንዳ ከ ታንዛንያ