ሰውነት ቢሻው ከኃላፊነታቸው ተነሱ

ሰውነት ቢሻው ከኃላፊነታቸው ተነሱ

ኢትዮጵያን ለ31 አመታት ወደራቀችበት የአፍሪካ መድረክ የመለሱት አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ከአሰልጣኝነት መንበራቸው መነሳታቸውን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡

በቻን ውድድር አንድም ግብ ሳያስቆጥር ከውድድሩ በጊዜ መውጣቱ እና የቅርብ ጊዜ ተከታታይ ውጤቶች ከውሳኔ ላይ እንዲደርሱ ምክንያት እንደሆናቸው የፌዴሬሽኑ አመራሮች ተናግረዋል፡፡

‹‹ አቶ ሰውነት በእግርኳሳችን ውስጥ የማይረሱ ጀግና ናቸው፡፡ ወደ እግርኳስ ካርታ እንድንመለስ ረድተውናል፡፡ አሰልጣኙ ባለፉት ሁለት አመታት ላስመዘገቡት ውጤት እውቅና እና ምስጋናችንን እናቀርባለን ፡፡ ነገር ግን በእድገታችን እና ውጤታማነታችን ለመቀጠል እዚህ ውሳኔ ላይ ደርሰናል›› ሲሉ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ጁይነዲ በሻ ገልጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ቀጣዩን አሰልጣኝ በ8 ቀናት ውስጥ እንደሚያሳውቅ የተነገረ ሲሆን ከሃገር ውስጥ እና ከውጪ ዜጋ አሰልጣኞች ውስጥ መስፈርቱን የሚያሟላ አሰልጣኝ እንደሚሾሙ ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል፡፡

አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በ2ኛ የስራ ጊዜያቸው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን ከቶም ሴይንትፌይት ተረክበው ከጥቅምት 2011 ጀምሮ ያሰለጠኑ ሲሆን በአጠቃላይ በውጤት ደረጃ በሁለት የሴካፋ ውድድሮች ተሳትፈው በአንዱ ሩብ ፍፃሜ ሲደርሱ በአንዱ ከምድብ ተሰናብተዋል፡፡ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎን ከ3 አስርታት በኃላ እነዲሁም ለመጀመርያ ጊዜ ለቻን ሲያደርሱ በአለም ዋንጫው ዋልያዎቹን ለፕሌይ ኦፍ ደረጃ አብቅተዋል፡፡