ታንዛኒያ የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ ቻምፒዮን ሆነች

 የሴቶች እግርኳስ | 10-01-2009 

በዩጋንዳ አስተናጋጅነት በጂንጃ ከተማ ሲደረገ የነበረው የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ ዛሬ ፍፃሜውን ሲያገኝ ታንዛኒያ ኬንያን 2-1 በማሸነፍ የውድድሩ ቻምፒዮን ሆናለች፡፡ ከፍፃሜ ጨዋታው አስቀድሞ ኢትዮጵያ ዩጋንዳን 4-1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የሶስተኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀች ሲሆን በምድብ ሁለት ከኢትዮጵያ ጋር ተደልድላ የነበረችው ታንዛኒያ በፍፃሜ ጨዋታው ባለድል ሆናለች፡፡

ሁለቱም ሃገራት ለዋንጫ ተጠብቀው ስለነበር የጨዋታው ግለት ከፍተኛ ነበር፡፡ የታንዛኒያ ተጫዋች የሆነችው ኦማሪ ማዋናሃሚሲ በ27ኛው እና 44ኛው ደቂቃ ያስቆጠረቻቸው ሁለት ግቦች የኪሊማንጃሮ ኩዊንሶቹን 2-0 መሪ ሆነው ወደ መልበሻ ቤት እንዲያመሩ አስችሏል፡፡ ኦማሪ በተደጋጋሚ በመጀመሪያው አጋማሽ የሃራምቤ ስታሬትሶችን የተከላካይ መስመር መፈተን የቻለች ሲሆን የመጀመሪው አጋማሽ ውጤት ሃገራቸውን ለማበረታታት ከኬንያ በእግርኳስ ፌድሬሽኑ እና በአቋማሪ ድርጅቱ ስፖርት ፔሳ አማካኝነት የመጡትን የኬንያ ደጋፊዎች አስቆጥቷል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ግብ ለማስቆጠር እና ውጤቱን ለመቀልበስ ወደ ሜዳ የተመለሱት ኬንያዎች በ48ኛው ደቂቃ ክርስቲን ናፉላ በግንባር በመግጨት ባስቆጠረችው ግብ መሪነቱን ማጥበብ ቢችሉም ዋንጫው ከማጣት ግን ሊድኑ አልቻሉም፡፡ ኢትዮጵያዊቷ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ወይንሸት አበራ ጨዋታውን ከመሩት ዳኞች መካከል ነበረች፡፡

ታንዛኒያ ከ30 ዓመታት በኃላ የተዘጋጀውን የሴቶች ሴካፋ ዋንጫ ቻምፒዮን ስትሆን ዛንዚባር ከ30 ዓመታት በፊት ውድድሩን ያሸነፈች መሆኑ ይታወሳል፡፡

ሰባት ሃገራት በውድድሩ ላይ የተካፈሉ ሲሆን የመወዳደሪያ ስፍራ እና የተጫዋቾች ማረፊያ በውድድሩ ላይ የታዩ ድክመቶች ናቸው፡፡ በአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ላይ ለምትሳተፈው ኬንያ ይህ ውድድር እንደጥሩ መዘጋጃ እንደሚሆናት የሚገመት ሲሆን አሰልጣኝ ዴቪድ ኦማ ከውድድሩ ቡድናቸው መልካም ተሞክሮ ማግኘት እንደሚችል ተነግሯል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *