ሊዲያ ታፈሰ የአለም ከ17 አመት በታች ሴቶች ዋንጫ ጨዋታዎችን በዳኝነት ትመራለች

  ቃለ መጠይቅ| 11-01-2009 

ኢንተርናሽናል አርቢቴር ሊዲያ ታፈሰ በጆርዳን አስተናጋጅነት በሚደረገው የአለም ከ17 አመት በታች ሴቶች ዋንጫ ላይ እንዲዳኙ ከተመረጡ ዳኞች አንዷ ሆናለች፡፡

የ2008 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ኮከብ ዳኛ ሆና የተመረጠችው ሊዲያ በዳኞች ዝርዝር ውስጥ የገባች ብቸኛዋ ኢትዮጵያዊት ስትሆን ከአፍሪካ ከተመረጡት 2 ዳኞች አንዷ ለመሆን በቅታለች፡፡ ሊዲያ በ2015 የካናዳ የአለም ሴቶች ዋንጫ ጨዋታዎች ላይም መዳኘቷ የሚታወስ ነው፡፡

የአለም ከ17 አመት በታች ሴቶች ዋንጫ በጆርዳን አስተናጋጅነት መስከረም 20 የሚጀመር ሲሆን ሊድያ ታፈሰ የፊታችን አርብ ወደ ጆርዳን የምታቀና ይሆናል፡፡

picsart_1474464726561

ሶከር ኢትዮጵያ ስለ ምርጫው ፣ ጉዞዋ እና ተያያዥ ጉዳዮች ከሊዲያ ታፈሰ ጋር ያደረገችውን ቃለምልልስ በዚህ መልኩ አቅርበነዋል፡፡

ኢትዮዽያውያን ዳኞች በኢንተርናሽናል መድረኮች ያላቸውን ተሳትፎ እንዴት ትመለከችዋለሽ?

አሁን ላይ በጣም የተሻለ ነገር አለ፡፡ ከዚህ ቀደም በነበረው የመታየት እድላችን አናሳ ነበር፡፡ ምክንያቱም ለሀገራት ምደባ ተብሎ አንድ ጨዋታ ነበር የሚመጣው፡፡ በአሁን ጊዜ ግን በአዲሱ አሰራር መሰረት የስፔን ፣ የፈረንሳይ ፣ የፖርቹጋል እና የእንግሊዝኛ ተናጋሪ ሃገራት በሚል ተከፋፍሎ በሚሰጡ ኮርሶች ላይ በምታሳየው ብቃት ብዙ የመታየት እድል ታገኛለህ፡፡ ስለዚህ አንድ ዳኛ ራሱን ለማብቃት ጠንክሮ ከሰራ ብዙ እርምጃ መራመድ ይችላል፡፡

በጆርዳን የአለም ከ17 አመት በታች ሴቶች ዋንጫ አላማሽ ምንድነው?

የተሻለ ነገር ለመስራትና ከምድብ ማጣሪያ ጨዋታ ውጭ ከሩብ ፍፃሜ አንስቶ እስከ ፍፃሜ ጨዋታ ድረስ ያሉትን ወሳኝ ጨዋታዎችን በብቃት ለመዳኘት በሚገባ ተዘጋጅቻለው፡፡

በዳኞቻችን አቅም ላይ ሁልጊዜም ጥያቄዎች ይነሳሉ. . .

እግር ኳስ በስህተት የተሞላ ነው፡፡ ስህተቱም ነው ውበት መሆን የሚችለው፡፡ በእኛ ሀገር ነው ከባድ የሚሆነው እንጂ በሌላው አለም ፕሮፌሽናል ዳኞች በታላላቅ ውድድሮች ላይ ትልልቅ ስህተቶችን ይፈፅማሉ ፤ ያውም ዘመናዊ መሳሪያዎች በተሟሉበት ሁኔታ፡፡ ነገር ግን እንደትልቅ ጉዳይ አይታይም፡፡ እኛ ሀገር ደግሞ ብዙ ነገሮች ባልተሟሉበት ሁኔታ ስህተት ይኖራል፡፡ ጥፋት የሚሆነው ስህተቱ ሲደጋገም ነው ። ከአንዱ ስህተት ወደ ሁለተኛው ሲኬድ እየታረመ መሄድ እንዳለበትና ስህተቶችን ተቀብለን ማረም እንዳለብን አምናለው፡፡ ነገር ግን ስህተት የእግር ኳስ ውበት እንደሆነ አምናለው ፤ ህዝቡም ሊቀበለው ይገባል፡፡

የዳኞቻችንን አቅም እንዴት ትገልጭዋለሽ ?

ጥሩ ነው፡፡ በአሁን ጊዜ አቅም ያላቸው ጥሩ ጥሩ ወጣት ዳኞች እየመጡ ነው፡፡ ሀገራችን ላይ ለዳኝነት የሚሰጠው ትኩረትና አስተሳሰብ በጣም የወረደ ነው፡፡ ሰዎች ወደዚህ ሙያ ለመምጣት ፍርሃት አላቸው፡፡ ዳኛ ላይ ያለው ስድብ ፣ ወቀሳ እና ውግዘት ስለሚበዛ አዳዲስ አቅም ያላቸው ዳኞችን ለማውጣት ያስቸግራል፡፡ በተቻለ አቅም ባሉን ኢንስትራክተሮች አማካኝነት ጥሩ ስራዎች እየተሰሩ ነው፡፡ ወደፊትም ጥሩ አቅም ያላቸው ዳኞች ይወጣሉ፡፡

picsart_1474464803946

በ2008 ኮከብ ዳኛ ሆነሽ ተመርጠሻል፡፡ የውድድር ዘመኑን እንዴት ታይዋለሽ ?

ለኔ ጥሩ የተሻለ አመት ነበር፡፡ በተመደብኩባቸው ጨዋታ ሁሉ ጥሩ ብቃቴን አሳይቻለው ብዬ አስባለው፡፡ በተለይ በሀዋሳ የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የማጠቃልያ ውድድር የፍፃሜው ጨዋታን በዙርያዬ ብዙ የተነሱ ነገሮች ነበሩ፡፡ እነዛን ለማጥፋት እና አቅሜን ማሳየት ስለነበረብኝ ያንን በተግባር ያሳየሁበት አመት ስለሆነ ከሽልማት በላይ የረካሁበት አመት ነበር ። ከሀገር ውጪ ደግሞ ካፍም ሆነ ፊፋ በመደቡኝ ጨዋታዎች ላይ ጥሩ ዳኝቻለሁ፡፡ ወደ ፖርችጋል ለ15 ቀን በመሄድ የአውሮፓ ቡድኖችን አጫውቻለው፡፡ ጥሩ ጊዜ ነበር፡፡

ወደፊት ወደ ዳኝነቱ መግባት ለሚፈልጉ ሴቶች ያለሽ መልእክት ምንድን ነው ?

ወደ ሙያው የሚገቡ አዳዲስ ዳኞችን በምችለው አቅም ለመደገፍ ዝግጁ ነኝ፡፡ አሁንም ቢሆን በማሰልጠን ከውጭ የማገኛቸውን ልምዶች በማካፈል ፣  ጨዋታዎችን በማየትና ምን ማድረግ እንደሚገባቸው በመንገር እያገዝኩ ነው፡፡ በተለይ አቅም ያላቸው ሴት ዳኞች እንዲበዙ የማስተላልፈው መልእክት ከክልል ፣ ከክፍለ ከተማ ፣ ከትምህርት ቤት ዳኞች መጥተው ስልጠና ከሚወስዱ ይልቅ በሴቶች እግር ኳስ ተጫውተው ያቆሙ  ተጫዋቾች የዳኝነት ኮርስ ቢወስዱ በጣም የተሻለ ነው፡፡ ምክንያቱም እግር ኳስ ምን እንደሚፈልግ ስለሚረዱ እና ልምድ ስላላቸው ወደዚህ ሙያ ቢመጡ መልካም ነው፡፡

በመጨረሻ…

ዳኝነት ትልቅ ስራ ነው ፤ ጥሩ ክፍያም አለው፡፡ ስለሆነም በማንበብ ፣ ስልጠናዎችን በመውሰድ እና ልምምድ በአግባቡ በመስራት የተሻለ ደረጃ መድረስ እንደሚቻል መልክቴ ነው፡፡

Leave a Reply