ሽመልስ በቀለ ለፔትሮጀት የ2016/17 የመጀመሪያ የሊግ ጨዋታውን አድርጓል

  ኢትዮጵያውያን በውጪ | 13-01-2009 

ኢትዮጵያዊው አማካይ ሽመልስ በቀለ በግብፅ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ፔትሮጀት ከአል ዳክልያ ጋር ከሜዳው ውጪ 1-1 በተለያየበት ጨዋታ ላይ ተሰልፎ መጫወት ችሏል፡፡

በክረምቱ በፔትሮጀት ያለውን ቆይታ ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት ያደሰው ሽመልስ በመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታ ክለቡ ፔትሮጀት ዋዲ ደግላን 1-0 ባሸነፈበት ጨዋታ በሶስት ቢጫ ምክንያት በቅጣት አልተሰለፈም ነበር፡፡

ሽመልስ በሁለተኛው አጋማሽ በ46ኛው ደቂቃ ዋኤል ፋራግን ቀይሮ ወደ ሜዳ የገባ ሲሆን ኤል ዳክልያ በጋናዊው ቤንጃሚን የ13ኛ ደቂቃ ግብ 1-0 መምራት ችለው ነበር፡፡ ሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ ሁለት ደቂቃ በኃለ በግራ መስመር ተጫዋቹ ኦሳማ መሃመድ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ ሁለቱ ክለቦች አቻ መሆን ችለዋል፡፡ ሽመልስ በ69ኛው ደቂቃ ከ16.50 ውጪ ያገኘውን ኳስ በጠንካራ ምት መትቶ በግቡ አናት የወጣበት ሲሆን በ78ኛው ደቂቃ ከናይጄሪያዊው ጄምስ ኦዎቦስኪኒ የተሻገረለትን ኳስ ወደ ግብ ሞክሮ የዳክልያ ግብ ጠባቂ መሃመድ ፋቲ አምክኖበታል፡፡ ባለሜዳዎቹ ከሽመልስ አስደንጋጭ ሙከራ በኃላ ፍፁም ቅጣት ምት ቢያገኙም አህመድ ሳሚር ፋራግ ምት በካሪም ታሪኪ ተመልሶበታል፡፡

የአቻ ውጤቱን ተከትሎ ፔትሮጀት በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ከሚገኘው አል አሃሊ በሁለት ነጥብ ብቻ በማነስ አራት ነጥብ መያዝ ችሏል፡፡

በሶስተኛ ሳምንት የግብፅ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ሐሙስ መስከረም 19 ፔትሮጀት በአል ስዌዝ ስታዲየም አስዋንን የሚገጥም ሲሆን በአል ሳላም ስታዲየም የኡመድ ኡኩሪው ኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢ ዓርብ መስከረም 20 አረብ ኮንትራክተርስን ያስተናግዳል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *