የአፍሪካ እግርኳስ | 15-01-2009
በኦሬንጅ 2016 የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የግብፁ ዛማሌክ እና የደቡብ አፍሪካው ማሜሎዲ ሰንዳውንስ የግማሽ ፍፃሜ ተጋጣሚዎቻቸውን በማሸነፍ ለፍፃሜ አልፈዋል፡፡ ዛማሌክ ዋይዳድ ካዛብላንካን 6-5 እንዲሁም ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ዜስኮ ዩናይትድን 3-2 በሆነ የአጠቃላይ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል፡፡
ፕሪቶሪያ ላይ በሚገኘው ሉካስ ሞርፒ ስታዲየም የተገናኙት ማሜሎዲ ሰንዳውንስ እና ዜስኮ ዩናይትድ ናቸው፡፡ ዜስኮ ዩናይትድ በመጀመሪያው ዙር ጨዋታ ንዶላ ላይ 2-1 ማሸነፍ የቻለ ሲሆን በመልሱ ጨዋታ ግን ብራዚሎቹ የጨዋታውን ውጤት መቀልበስ ችላዋል፡፡ 2-0 በተጠናቀቀው ጨዋታ ላይቤሪያዊው አንቶኒ ላፎር እና ፔርሲ ታኦ ግቦቹን ከመረብ አሳርፈዋል፡፡ የካማ ቢሊያት እና ኪገን ዶሊ ቅንጅት ለዜስኮ ተጫዋቾች የራስ ምታት ሆኖ አልፏል፡፡
ዛማሌክ በሞሮኮ መዲና ራባት ላይ በዋይዳድ ካዛብላንካ 5-2 ቢሸነፍም የመጀመሪያው ዙር ላይ 4-0 በማሸነፉ ወደ ፍፃሜው ማለፍ ችሏል፡፡ ዋይዳድ በብዙዎች ያልታሰበውን ውጤት የመቀልበስ ስራ ቢሰራም በስተመጨረሻ ሳይሳካለት ቀርቷል፡፡
የካዛብላንካው ክለብ ዌልሳዊውን አሰልጣኝ ጆን ቱሻክን አሰናብቶ የቀድሞ ተጫዋቹን ሙሃመድ ሳሂልን ቀጥሯል፡፡ በኮምፕሌክስ ስፖርቲፍ ሞላይ አል ሃሰን ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ከአውሮፓ በዓመቱ መጨረሻ ዋይዳድን ተቀላቀለው ላይቤሪያዊው ዊሊያል ጄቦር እና የኮንጎ ብራዛቪል ኢንተርናሽናል የሆነው ፋብሪስ ኦንዳማ ሁለት ሁለት ግብ ሲስቆጥሩ ኢስማኤል ኤል ሃዳድ አንድ ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡ የዛማሌክ ሁለት ግቦች ባሰም ሙርሲ እና ዋዲ ደግላን ለቆ በክረምቱ የዝውውር መስኮት ወደ ካይሮ ሃያሎቹ የተዛወረው ናይጄሪያዊው ስታንሊ ኦሃዉቺ አስቆጥረዋል፡፡
ዛማሌክ ከ14 ዓመታት በፊት ሌላኛውን የካዛብላንካ ክለብ ራጃ ካዛብላንካን በማሸነፍ ለአምስተኛ ግዜ የአፍሪካ ሻምፒዮን መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡ የቀድሞ የባፋና ባፋና አሰልጣኝ ፒትሶ ሞሴሚኒ ሰንዳውንስ ለደቡብ አፍሪካ አብሳ ፕሪምየርሺፕ ሻምፒዮንነት ያበቁ ሲሆን ከኦርላንዶ ፖይሬትስ በመቀጠል የቻምፒየንስ ሊጉ ዋንጫን ያገኘ ሁለተኛው የደቡብ አፍሪካ ክለብ ለመሆን በፍፃሜው ዛማሌክን ይገጥማሉ፡፡
የዛማሌክ እና የማሚሎዲ ሰንዳውንስ የፍፃሜ ጨዋታ የመጀመሪያ ዙር ጥቅምት 4 2009 እንዲሁም ለመልሱ ጨዋታ ጥቅምት 11 እንደሚደረግ የካፍ ፕሮግራም ያሳያል፡፡
የጨዋታ ውጤቶች፡
ዋይዳድ ክለብ አትሌቲክ (ሞሮኮ) 5-2 ዛማሌክ (ግብፅ) [5-6]
ማሜሎዲ ሰንዳውንስ (ደቡብ አፍሪካ) 2-0 ዜስኮ ዩናይትድ (ዛምቢያ) [3-2]