ዩጋንዳዊው ኪሪዚስቶም ንታምቢ ለጅማ አባቡና ፈርሟል

  ዝውውር | 17-01-2009 

የ25 ዓመቱ ዩጋንዳዊ የአማካይ ስፍራ ተጫዋች ኪሪዚስቶም ንታምቢ የፕሪምየር ሊጉን አዲስ ክለብ ጅማ አባቡናን እንደተቀላቀለ የሚወጡ መረጃዎች ጠቁመዋል።

ተጫዋቹ ያለፈውን ዓመት በደቡብ አፍሪካ ሁለተኛ ዲቪዝዮን ለሚወዳደረው ቫስኮ ደጋማ ክለብ በመጫወት ያሳለፈ ሲሆን በተመሳሳይ የአንድ ዓመት ውል ነው ለጅማ አባቡና የፈረመው።

ንታምቢ በሃገሩ ዩጋንዳ ለቪላ ስፖርት ክለብ አካዳሚ፣ ለጆጎ ክለብ ወጣት እና ዋናው ቡድን ተጫውቶ ያሳለፈ ሲሆን በቪዬትናም ሊግ ተሳታፊ ከነበረው ናቪባንክ ሳይጎን ክለብ ጋርም ቆይታ ነበረው።

ለዩጋንዳ ከ20 ዓመት በታች ቡድን ተጫውቶ ያሳለፈው ንታምቢ ዋናው ብሔራዊ ቡድን በግንቦት 2015 ናይጄሪያን 1-0 ባሸነፈበት ጨዋታ ላይ ተጠባባቂ ከመሆን ባለፈ እስካሁን የመጫወት ዕድል አላገኘም።

አሠልጣኝ ሚሉቲን ሰርዶጄቪች ሚቾ ትልቅ ግምት በሚሰጡት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጥሩ አቋም ማሳየት ከቻለ ግን በዓመቱ አጋማሽ ጋቦን ላይ በሚደረገው የ2017ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የሚሳተፈው የኡጋንዳ ብሔራዊ ቡድን አባል ሊሆን ይችላል ተብሎ ይጠበቃል።

ጅማ አባ ቡና ጀማል ጣሰው ፣ ቢንያም አሰፋ ፣ መሃመድ ናስር እና በድሉ መርዕድን የመሳሰሉ የፕሪሚየር ሊግ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾችን በማስፈረም ስብስቡን ማጠናከር ችሏል፡፡

1 Comment

Leave a Reply