ዝውውር | 17-01-2009
የቀድሞው የብሩንዲ ብሔራዊ ቡድን አጥቂ ዲዲዬ ካቩምባጉ ኤሌክትሪክን በነፃ ዝውውር ተቀላቅሏል።
ከክለቡ ባገኘነው መረጃ መሠረት ካቩምባጉ ለቀጣይ 6 ወራት በኤሌክትሪክ የሚጫወት ሲሆን ከለቡ የተጫዋቹን አቋሙ አይቶ ለተጨማሪ ጊዜ የሚያቆይበት ውል የማስፈረም መብቱ አለው።
የ28 ዓመቱ አጥቂ በሃገሩ ብሩንዲ ለአትሌቲኮ ኦሎምፒክ የተጫወተ ሲሆን በብሩንዲ ብሔራዊ ቡድን እና በ2012ቱ የሴካፋ ክለቦች ዋንጫ ባሳየው አቋም በወቅቱ የታንዛኒያው ክለብ ያንግ አፍሪካ አሰልጣኝ የነበሩትን ቶም ሴንትፊት ትኩረት መሳብ ችሏል። ካቩምባጉ በ4 ዓመት የታንዛኒያ ቆይታው ለያንግ አፍሪካ እና አዛም ክለቦች ተጫውቶ አሳልፏል። በያንጋ በ63 ጨዋታዎች 31 ግቦች ከመረብ ሲያሳርፍ በአዛም 40 ጨዋታዎችን አድርጎ 15 ግቦች ማስቆጠር ችሏል፡፡
ተጫዋቹ ከአዛም ክለብ ጋር ከተለያየ በኋላ በዓመቱ መጨረሻ ወደ ቪዬትናም በማቅናት የሙከራ ጊዜ ያሳለፈ ቢሆንም ክለብ ማግኘት አልቻለም ነበር።
ከካቩምባጉ በተጨማሪ ዳዊት እስጢፋኖስ እና ሙሉአለም ጥላሁንን ያስፈረመው ኤሌክትሪክ ከተስፋ እና 17 አመት በታች ቡድኑ 9 ተጫዋቾችን በማሳደግ በአዲስ ገጽታ የውድድር ዘመኑን ይጀምራል፡፡