የአፍሪካ እግርኳስ | 18-01-2009
ጋቦን በጥር 2017 ለምታስተናግደው የቶታል አፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ ሃገራት የምድብ ቋታቸውን አውቀዋል፡፡
ብቸኛዋ የምስራቅ አፍሪካ ተሳታፊ ሃገር ዩጋንዳ ቋት 4 ላይ ስትመደብ ቋት 1 ላይ አዘጋጇ ጋቦን፣ የ2015 የአፍሪካ ሻምፒዮኗ ኮትዲቯር፣ ጋና እና አልጄሪያ ሆነዋል፡፡
ቋት ሁለት ላይ የ2004 የአፍሪካ ሻምፒዮኗ ቱኒዚያ፣ ማሊ፣ የ2013 የፍፃሜ ተፋላሚዋ ቡርኪናፋሶ እና ዲ.ሪ. ኮንጎ ሁነዋል፡፡
ቋት ሶስት ላይ፡ የ2002 ሻምፒዮኗ ካሜሮን፣ ሴኔጋል፣ ሞሮኮ እና የሰባት ግዜ የአህጉሪቱ ታላቅ ውድድር አሸናፊ ግብፅ ሲሆን የመጨረሻው ቋት ዩጋንዳ፣ ቶጎ፣ ዚምባቡዌ እና የመጀመሪያ ግዜ ተሳታፊ የሆነችው ጊኒ ቢሳው ሁነዋል፡፡ ቋቱ በአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅ ኮሚቴ በካፍ ዋና ፅህፈት ቤት ካይሮ ላይ ሰኞ ዕለት ፀድቋል፡፡
የቋት ደረጃው የወጣው በባለፉት ሶስት ተከታታይ የአፍሪካ ዋንጫ የቡድኖቹ ውጤቶች፣ በ2013፣ 2015 እና 2017 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ውጤቶች፣ በ2014 የፊፋ የአለም ዋንጫ ውጤቶች እንዲሁም በ2014 የፊፋ የአለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ናቸው፡፡ በዚህም መሰረት የምድብ አንድ አባት ጋቦን ስትሆን የ2015 ሻምፒዮኗ ኮትዲቯር የምድብ ሶስት አባት ሁናለች፡፡ የምድብ ሁለት እና አራት የምድብ አባቶችን ለመለየት በጋና እና አልጄሪያ መካከል ዕጣ የሚወጣ ይሆናል፡፡ በተመሳሳይ ቋት ላይ የሚገኙ ሃገራት አንድ ላይ በምድብ ውስጥ አይመደቡም፡፡
የአፍሪካ ዋንጫው የምድብ ድልድል በጋቦን ርዕሰ መዲና ሊበርቪል ላይ በፈረንጆቹ ጥቅምት 19 ሲወጣ ውድድሩ ከጥር 14 – መጋቢት 5 2017 በሊበርቪል፣ ፍራንስቪል፣ ኦየም ቢተም እና ፖርት ጀንትል ከተሞች ይካሄዳል፡፡