ናኦሚ ግርማ ፡ ኢትዮ-አሜሪካዊቷ በዓለም ዋንጫ. . .

  ኢትዮጵያውያን በውጪ | 18-01-2009 

በአለም ከ17 አመት በታች ዋንጫ የሚካፈለው የዩናይትድ ስቴትስ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ቢጄ ስኖው ወደ ጆርዳን ይዘዋቸው ከተጓዙ 21 ተጫዋቾች መካከል ከኢትዮጵያውያን ወላጆቿ የተወለደችው ናኦሚ ግርማ ትገኝበታለች፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ ከሚተማመንባቸው ተጫዋቾችም አንዷ ናት፡፡

ናኦሚ በግራናዳ አስተናጋጅነት በተካሄደው የ2016 ኮንካካፍ ከ17 አመት በታች ሴቶች ዋንጫ ላይ አሜሪካ ባደረገቻቸው 5 ጨዋታዎች ላይ እያንዳንዷን ደቂቃ ተጫውታለች፡፡ ቡድኑ የውድድሩ አሸናፊ ሆኖ ለአለም ከ17 አመት በታች ዋንጫ እንዲያልፍ ከረዱት ተጫዋቾችም አንዷ የነበረች ሲሆን የውድድሩ ምርጥ 11 ውስጥም ተካታለች፡፡

አምና በU-15, በ2015 ደግሞ በU-14 ብሄራዊ ቡድኖች ተጫውታ ያሳለፈችው ናኦሚ በ2016 የውድድር ዘመን 13 ጨዋታዎችን (1106 ደቂቃዎች) ለ17 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን በመጫወት ከሁሉም የቡድን አባላት ቀዳሚ ናት፡፡

picsart_1475058130275

የዩናይትድ ስቴትስ የእግርኳስ ብሄራዊ ቡድን ድረ ገጽ “ዩኤስሶከር” ስለ ብሄራዊ ቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾች ባስነበበው ፅሁፍ የሴንትራል ቫሊ ክሮስፋየር ክለብ ተከላካይ የሆነችው ናኦሚን እንዲህ ይገልፃታል፡፡ ” ከሜዳ ውጪ ደግ ፣ ተግባቢ እና የምጡቅ አእምሮ ባለቤት ናት፡፡ ሜዳ ላይ ደግሞ ፈጣን ፣ ጉልበተኛ እና በራስ መተማመን ያላት ናት” ይላታል፡፡ “ሁልጊዜም ከባዱን መሞከር” የናኦሚ ባህርይ ነው፡፡ ይህንንም በልጅነቷ ከእድሜ ታላላቆቿ ጋር እግርኳስን በመጫወት አዳብራለች፡፡

” እግርኳስን መጫወት የጀመርኩት በ5 አመት እድሜዬ ነው፡፡ ወንዶች እና ሴቶች በጋራ እግርኳስን እንጫወት ነበር፡፡ እንደየእድሜያችን ተከፋፍለን ብንጫወትም የእኔ ምርጫ ሁልጊዜም ከታላላቆቼ ጋር መጫወት ነበር፡፡ ቤተሰቦቼም ይፈቅዱልኝ ነበር፡፡ ”

picsart_1475058239498

ቤተሰብ ፣ ማንነት እና ኢትዮጵያ

የናኦሚ አባት ግርማ አወቀ የተሻለ ኑሮ እና ትምህርት ፍለጋ የዩናይትድ ስቴትስ ምድርን የረገጠው እ.ኤ.አ በ1982 ነበር፡፡ ግርማ እንዳሰበውም ኢንጂነሪንግ የመጀመርያ ዲግሪውን ከሳን ሆዜ ዩኒቨርሲቲ ተቀብሏል፡፡ እናቷ ሰብለ ደምሴ ደግሞ ወደ አሜሪካ ያቀናችው በ1987 ነበር፡፡ በአሜሪካ የተዋወቁት ሁለቱ ጥንዶች በ1995 ተጋብተው ፤ ግርማ በህክምና ኢንጂሪንግ ፣ ሰብለ ደግሞ በፋይናንስ ዘርፍ ተሰማርተው ፤ ናትናኤል እና ናኦሚ የተባሉ ሁለት ልጆች ወልደው በሳን ሆዜ ኑሯቸውን መሰረቱ፡፡ ከ16 አመታት በኋላም ናኦሚ በአሜሪካ ከ17 አመት በታች ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ተጫዋቸነት በአንዳንድ ጨዋታዎችም በአምበልነት ራሷን አገኘች፡፡

የናኦሚ አባት ግርማ አወቀ በሳን ሆዜ የኢትዮጵያውያንን ግንኙነት ለማጠናከር “ማለዳ ሶከር” የተሰኘ ማህበር ከመሰረቱት መካከል አንዱ ነው፡፡

picsart_1475057314723

ናኦሚ አስተዳደጓ ራሷን አሜሪካዊ አድርጋ እንድትቆጥር ቢያደርጋትም ለቤተሰቦቿ ባህል እና ማንነት ትልቅ ቦታ እንደምትሰጥ ትናገራለች፡፡ ቤተሰቦቿ ያስተማሯት አማርኛ ቋንቋንም በሚገባ ትናገራለች፡፡

” ያደግኩት በዩናይትድ ስቴትስ ነው፡፡ ነገር ግን ስለ ቤተሰቦቼ ሀገር ያለኝን እይታ አጥቼ አላውቅም፡፡ ዩናይትድ ስቴትስን ወክዬ በመጫወቴ ከፍተኛ ክብር እና ኩራት ይሰማኛል፡፡ ነገር ግን ቤተሰቦቼ ለተሻለ ኑሮ በተጓዙበት መንገድም ኩራት ይሰማኛል፡፡ ” ትላለች፡፡

ወደ 6ኛ ክፍል ከመግባቷ በፊት ባለው ክረምት ወደ ኢትዮጵያ መምጣቷን የምትናገረው ናኦሚ እናቷ ያደገችበት አዲስ አበባ እና የአባቷን የትውልድ ቦታ አዳማን አይታለች፡፡ አያቷን በህይወት የማግኘት እድልም አግኝታለች፡፡ በኢትዮጵያ የአንድ ወር ቆይታዋ ፍጹም የተለያየ ባህል ውስጥ መገኘቷ ቢያስደነግጣትም በህዝቡ እና በምግቡ ደስተኛ ነበረች፡፡

” ካደግኩበት ሀገር ስወጣ ይህ ለመጀመርያ ጊዜ ነበር፡፡ እናም አስደናቂ ተሞክሮ አግኝቼበታለሁ፡፡ ነገር ግን አስከፊ ነገሮችም አይቻለሁ፡፡ ወላጆቼ ያደጉበትን አካባቢ ስመለከት ለኛ ጥሩ ህይወት መኖር ምን ያህል ጠንክረው እንደሚሰሩ ተረድቻለሁ፡፡ ”

ናኦሚ ከዩናይትድ ስቴትስ የኢትዮጵያውያን ኮሚኒቲ ጋር የጠበቀ ግንኙነት አላት፡፡  የኢትዮጵያ በአላትንም በኢትዮጵያዊ ምግብ እና አለባበስ ከኮሚኒቲው ጋር በጋራ ታከብራለች፡፡ ክትፎ እና ጥብስ ደግሞ ከባህላዊ ምግቦች የምትወዳቸው ናቸው፡፡

በልጅነቷ ተጫውታ ያለፈችበት እና በአባቷ አማካኝነት የተመሰረተው ማለዳ ሶከር ሁልጊዜም በልቧ አለ፡፡ ያደገችበት አካባቢ እና የኢትዮጵያ ኮምዩኒቲም ከአካባቢው ወጥታ ዩናይትድ ስቴትስን መወከል በመቻሏ ኩራት ተሰምቷቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ሴቶች ብሄራዊ ቡድን በካሜሩን ተሸንፎ ከአለም ዋንጫው በመቅረቱ በጆርዳን አስተናጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው የአለም ከ17 አመት ሴቶች ዋንጫ የኢትዮጵያን ስም ሊያስጠሩ የሚችሉት ናኦሚ ግርማ እና አርቢቴር ሊዲያ ታፈሰ ብቻ ናቸው፡፡

picsart_1475058206630

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *