ዮርዳኖስ አባይ ጫማውን ሰቀለ

በኢትዮጵያ የውስጥ ውድድሮች ረጅም አመታት ባይጫወትም ዝናው የናኘ ድንቅ አጥቂ ነበር፡፡ ለ3 ተከታታይ አመታት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ኮከብ ግብ አግቢ የነበረው በየመን ለ10 አመታት ከተጫወተ በኋላ ከጨዋታ አለም ለመገለል ወስኗል፡፡ በአልሳቅር ክለብ ውስጥ ልዩ ስፍራ የሚሰጠው ድንቅ አጥቂ የተገኘው ከእግርኳስ ቤተሰብ ነው፡፡ አባቱ አባይ ጌታሁን በድሬዳዋ ጨርቃ ጨርቅ በ1960ዎቹ ድንቅ አገልግሎት ያበረከቱ ምርጥ ግብ አስቆጣሪ የነበሩ ሲሆን ታላቅ ወንድሙ ስምኦን አባይ በታላላቆቹ መብራት ኃይል እና ኢትዮጵያ ቡና ምርጥ አመታትን ያሳለፈ አጥቂ ነው፡፡ በ1991 በድሬዳዋ ጨርቃጨርቅ እግርኳስ መጫወት የጀመረው ‹‹ ቡሎ ›› ዝናው ወደናኘበት መብራት ኃይል ያመራው በ1992 አም. ነው፡፡ በዛኑ አመት ብዙ የመሰለፍ እድል ባያገኝም 7 ግቦችን ከመረብ አሳርፏል፡፡

በዮርዳኖስ አባይ የእግርኳስ ህይወት ውስጥ ትልቅ አሻራ ጥሎ ያለፈው አመት 1993 ነው፡፡ ከመብራት ኃይል ጋር በኢትዮጵያ የተዘጋጁትን ሁሉንም ውድድሮች በዋንጫ ድል ሲደመድም በግሉ እስካሁን ያልተደፈረ 24 ግብ አስቆጥሮ የሊጉ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኗል፡፡ ከኢትዮጵያ ወጣት ቡድን ጋር በአፍሪካ ወጣቶች ዋንጫ ቡድናችን ግማሽ ፍፃሜ በመግባት ለ2001 የአለም ወጣቶች ዋንጫ እንዲያልፍ ጉልህ ሚና ተጫውቷል፡፡

በ1996 ኢትዮጵያን ለቆ ወደ የመኑ አልሳቅር በተሸገረ የመጀመርያው የውድድር ዘመኑ የየመን ሊግ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ ሲያጠናቅቅ በአጠቃላይ በየመን በቆየባቸው አመታት የክለቡ የምንግዜም ግብ አግቢ ለመሆን በቅቷል፡፡

ዮርዳኖስ አባይ በድሬዳዋ ጨርቃጨርቅ ፣ መብራት ኃይል ፣ ኢትዮጵያ ቡና ፣ አልሳቅር ፣ የኢትዮጵያ ወጣት እና ዋናው ብሄራዊ ቡድን ጣፋጭ 15 አመታትን ካሳለፈ በኃላ ከጨዋታ አለም መገለሉን አስታውቋል፡፡ አልሳቅር ክለብም ለድንቅ ተጫዋቻቸው ክብር መሸኛ ፕሮግራም ያዘጋጁለት ሲሆን በክለቡ ውስጥ በአሰልጣኝነት ወይም በዳይሬክተርነት እንዲቀጥል ከክለቡ ጥያቄ ቀርቦለታል፡፡

{jcomments on}

ያጋሩ